በክልሎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል--የፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በክልሎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል--የፌዴሬሽን ምክር ቤት

ሀዋሳ ሰኔ 3/2014 (ኢዜአ) በክልሎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የአጎራባች ክልሎች የጋራ ፎረም አስተዋጽኦ እንደሚያበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
የኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ ህዝቦችና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ክልል አጎራባች መንግስታት ግንኙነት ፎረም ለመመስረት የሚያስችል መድረክ በሃዋሳ አካሂደዋል።
በመድረኩ ከክልሎቹ የተውጣጣ የጋራ ፎረም መስራች ኮሚቴም ተቋቁሟል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዛሕራ ሁመድ እንዳሉት ምክር ቤቱ በህዝቦች መካከል በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ክልሎች በመካከላቸው ችግሮቻቸውን፣የልማት ሥራዎችንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በጋራ የሚያካሂዱባቸው የአጎራባች ክልሎች የጋራ መድረክ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ አለመግባባቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ዘመናዊና ባህላዊ የግጭት መከላከያና ማስወገጃ ስልቶችን በማጥናት፣ የአሰራር ስርዓትና ስልት በመዘርጋት ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።
“ክልሎች ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ የተገኘውን ሁለንተናዊ ለውጥ ሚዛኑን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚቻለው የፌዴራል ስርዓቱን በማጠናከር በኩል የሚካሄዱ የጋራ መድረኮች ለዴሞክራሲ ግንባታ ፋይዳቸው የጎላ ነው” ሲሉ ተናግርዋል።
አራቱ ተጎራባች ክልሎች በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፣ ይህን በጋራ የመኖር እሴት እንዲጠናከር አሳስበዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት የአጎራባች ክልሎች የጋራ ፎረም አስተዋጽኦው የላቀ ነው ብለዋል።
“ክልሎቹ በጋራ በመመካከርና አብሮ በመስራት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ልማትን አብሮ የማካሄድ ተግባራት ሲከናወኑ ውጤታማ እንሆናለን ” ነው ያሉት።
ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት ለማረጋገጥ የጋራ መድረክ እየፈጠሩና እየተመካከሩ መስራት ወሳኝ መሁኑንም አመላክተዋል።
ፎረሙ የልማት፣ የሰላም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በትኩረት ለማከናወን ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ደስታ ገልጸዋል።
በመድረኩ የአራቱ ክልሎች የጋራ ፎረም ለመመስረት ዝግጅት የሚያደርጉ ከ4 ክልሎች አንድ አንድ ተወካዮችና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት የዴሞክራሲያዊ አንድነትና ንቃተ ህገ መንግሥት ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አባል የሆኑበት ኮሚቴ ተቋቁሟል።
በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት የሚካሄደው የመጀመሪያውን የክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች የጋራ መድረክ የጋራ ኮሚቴው ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ እንደሚያካሂድ ተገልጿል።
መድረክ ላይ የአራቱ ክልሎች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችና ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።