የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት ከጎረቤቶቻችን ለይተን የማናየው በመሆኑ ለቀጣናዊ ትስስር በጋራ እንሰራለን--ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

376

ሰኔ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት ከጎረቤቶቻችን ለይተን የማናየው በመሆኑ ለቀጣናዊ ትስስር በጋራ እንሰራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሸክ ሞሀመድ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በሶማሊያ ፖለቲካ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መደረጉን አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሊያ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረና በህዝብ ለህዝብ ትስስር ጭምር የተጠናከረ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን ይህ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያረጋገጡት፡፡

ኢትዮጵያ የምታካሂደውን ልማትና የሰላም ግንባታ ከጎረቤቶቿ ለይታ አታየውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከዚህ አኳያ የቀጣናው አገራት ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም "ያሉንን ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅሞች ለቀጠናው ትስስር መጠቀም አለብን" ብለዋል፡፡"የጎረቤቶቻችን ሰላም ለኢትዮጵያ ብልጽግና ወሳኝ ሚና አለው፤ የኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ለመልማት ቁርጠኛ ናት" ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

በመጨረሻም ለአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሸክ ሞሀመድ ስልጣን ዘመን የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በሶማሊኛ ቋንቋ ለሶማሊያ ህዝብ ያስተላለፉት መልዕክት በበርካታ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም