ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በሚጠናከርበት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ገለፀ

አዲስ አበባ  ጳጉሜን 5/2010 በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በሚጠናከርበት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የተሰኘው የፖለቲካ ማህበር አስታወቀ። ንቅናቄው በስደት ውጭ አገር ሆኖ በኢትዮጵያ ይፈፀማሉ ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመቃወም ሲንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት ነው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎም መስራቹን አቶ ኦባንግ ሜቶን ጨምሮ 15  አባላት ያሉት የንቅናቄው ልኡካን ቡድን ጳጉሜ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ወደአገር ቤት መግባቱ ይታወሳል። የንቅናቄው አባላት ወደአገር ቤት የመጡት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ነው። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ዛሬ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ወይይት አድርገዋል። "ወደኢትዮጵያ የመጣነው በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝና የፖለቲካ ሁኔታ ለመገመግም ነው" ሲሉ አቶ ኦባንግ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል። "ከዘር፣ ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ቅድሚያ ሰብዓዊነት ይበልጣል" ያሉት አቶ ኦባንግ ንቅናቄው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ የዜጎችን እኩልነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በየአካባቢው በተነሱ ግጭቶች ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን ችግር ለመቅረፍም ከመንግስት ጋር የሚሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም ለንቅናቄው ተግባራት ትብብር እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት አመልክተዋል። ያለፈውን ነገር በማንሳት ወደአላስፈላጊ ሁኔታ ከመግባት ይልቅ ይቅር በመባባል በትብብር በቀጣይ ኢትዮጵያ የምታድግበት ጉዳት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሚያስፈልግ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም