በአጎራባች አከባቢዎች የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ትስስር መጎልበት የህብረተሰቡን ማህበራዊ ትስስር እያጠናከረው ነው

350

ባህር ዳር ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) በአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አጎራባች አከባቢዎች የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ትስስር የማጎልበት ተግባር የህዝቡን አብሮነት እያጠናከረው መሆኑ ተገለጸ።

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዚገም ወረዳ "ቅላጅ" ከተማ ህግ የማስከበር ዘመቻውን ለመደገፍ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት አመራሮቹ ለኢዜአ እንዳሉት፣ የህወሓትን ተልዕኮ ተሸክመው በሚንቀሳቀሱ ጥቅመኞች በንጹሀን ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲያደርሱ ቆይቷል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አፈ ጉባኤ ሙሉአዳም እጅጉ እንደገለጹት፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ልዩነት ሳይገድባቸው በሀዘንም፤ በደስታም በአብሮነት ተሳስረው የሚኖሩ ናቸው።

ለበርካታ አመታት በተዘራ የጥላቻ ሀሳቦች ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ንጹሃን ዜጎች ጭምር ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

የተከሰተው ችግር የአካባቢው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጭምር  መጎዳቱን ነው ያመላከቱት።

"እርስ በርስ በመጋጨት ማንም አትራፊ እንደማይሆን የገለጹት ለአንድነትና አብሮነት በጋራ መስራት እንደሚገባ እስገንዝበዋል።

በህዝቦች መካከል የተፈጠረውን የሻከረ ግንኙነት ለመመለስ የህዝብ ለህዝብ ትስስሮችን የሚያጎለብቱ ሥራዎች በስፋት መሰራቱን ጠቁመው፣ በእዚህም የሁለቱን ህዝቦች የቀደመ መልካም ግንኙነት ለመመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

ለመገበያየት ከአንዱ ክልል ወደ ሌላኛው ከመሄድ ባለፈ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በአብሮነት እያከናወኑ መሆኑን አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዳንጉር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ክንፉ በበኩላቸው የ"ጉህዴን" አማጺ ቡድን  የሀገር አፍራሽ ቡድኖችን ሴራ ለማስፈፀም በአካባቢው ሲንቀሳቀስ እንደነበር ገልጸዋል።

በእዚህም የለቱ ማህበረሰብ በጋራ እንዳይኖር በርካታ እኩይ ድርጊቶች መፈጸሙን ነው የተናገሩት።

የህወሓት አጀንዳዎችን ተቀብሎ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረው አብሮነት እንዲናድ በፈጸመው ጥፋት ዜጎች ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበረም አስታውሰዋል።

"በአሁኑ ወቅት የጠላቶች የጥፋት ሴራ በመክሸፉ የህዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቷል" ብለዋል።

ህዝቡ የጥፋት ቡድኖችን እኩይ ሴራ ተረድቶ ለነሱ አጀንዳ መጠቀሚያ እንዳይሆን የተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም የእርስ በርስ ግንኙነቱን ማጠናከሩን ነው ያመላከቱት።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የጠላትን ሴራ በማክሸፍ በጋራ የማይቋረጥ አብሮ የመኖር እሴት እንዲቀጥል ማድረጉንም ተናግረዋል።

የአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮችና አጎራባች ዞኖች የህዝቦችን በጋራ አብሮ የመኖርና የመልማት እሴት አጠናክሮ ለማስቀጠል ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም