የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በአባይና አዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል

385

ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በአባይና አዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ዜጎች ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስገነዘበ፡፡

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በመጪው ክረምት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል፡፡

ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወንዝ አመራር ቡድን መሪ ተመስገን ከተማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተለይ በላይኛው አዋሽ ተፋሰስ እና የአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

በተጠቀሱት የተፋሰሱ አካባቢዎች ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችልም ነው የጠቆሙት፡፡

ይህን ተከትሎም መንግሥት አስቀድሞ የጎርፍ አደጋን መከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

ከፍተኛ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች የሚገኙ ግድቦች ከአቅማቸው በላይ ሞልተው የጎርፍ አደጋ እንዳያስከትሉ የያዙትን ውሃ ሕብረተሰቡን በማይጎዳ መልኩ የመቀነስ ሥራ እንደሚከናወንም ነው ያብራሩት።

ደለል የማጽዳት እንዲሁም ውሃው ከወንዝ አቅጣጫው እንዳይወጣ የማድረግ ሥራ በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ከሚገኙ የጥንቃቄ ሥራዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመንግሥት ከሚከናወኑ የጥንቃቄ ሥራዎች በተጨማሪ በተደጋጋሚ ጎርፍ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ሕብረተሰቡ ሳይዘናጋና ራሱን ለአደጋ በማይጥል መልኩ የጥንቃቄ ተግባራትን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በክረምቱ ወቅት በተለይ በአባይ የተፋሰስ አካባቢ እንደሚኖር የሚጠበቀው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት ሥራ በጎ ሚና እንደሚኖረውም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም