የቴሌብር የክፍያ ሥርዓት በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እንዲጎለብት የበኩሉን ሚና እያበረከተ ነው

75

ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) የቴሌብር የክፍያ ሥርዓት በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እንዲጎለብት የበኩሉ ሚና እያበረከተ መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮም እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት ክፍያን በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮ-ቴሌኮም  ዋና ሥራ  አስፈጻሚ  ፍሬህይወት  ታምሩ እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ብሩህተስፋ ሙሉጌታ ናቸው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ  ዜጎች አዲስ  ፓስፖርት ለማውጣት፣ ለማሳደስና  የጠፋን  ፓስፖርት  ለመተካት   የሚጠበቅባቸውን  የአገልግሎት ክፍያ በቴሌብር አማካኝነት እንዲከፍሉ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ይህም የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ጊዜና ሃብትን ከብክነት ያስቀራል ብለዋል፡፡

የቴሌብር የክፍያ ሥርዓት በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እንዲጎለብት የበኩሉን ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ አገልግሎቱ በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ 20 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራት ተችሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም እስካሁን ባለው ሂደት በቴሌብር አማካኝነት 20  ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዝውውር መደረጉን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ኢትዮ-ቴሌኮም የተለያዩ ተቋማት የቴሌብር  የክፍያ ሥርዓትን እንዲጠቀሙ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ብሩህተስፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ የክፍያ ሥርዓቱ ተቋሙ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በፍጥነት ተደራሽ እንዲያደርግ እንደሚያስችለው አብራርተዋል፡፡

በተለይ ከፓስፖርት ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም እንግልትን እንደሚቀርፍም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም