ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የበጎ አድራጎት ተግባርና ሀገራዊ ለውጡን እንደሚያጠናክሩ በወላይታና በኦሶሳ ነዋሪዎች ገለጹ

ሶዶ/አሶሳ  ጶግሜ 5/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የበጎ አድራጎት ተግባርና ሀገራዊ ለውጡን  በማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በወላይታና አሶሳ ነዋሪዎች  ገለጹ፡፡ የወላይታ ዞን አስተዳደር ደግሞ በዓሉን ምክንያት በማድረግ  ወላጆቻቸውን ላጡ  ከ100 በላይ ለሚሆኑ ችግረኛ ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደርጓል፡፡ በሶዶ ከተማ መርካቶ ክፍለ ከተማ የአረጋዊያንን ቤት ሲጠግን የኢዜአ  ሪፖርተር ያነጋገረው ወጣት አብነት ምንተስኖት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የምህንድስና ተማሪና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ነው፡፡ ከሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ጋር ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሄዶ መመጣቱን ገልጾ ይህም  " ሃገራዊና የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል "ብሏል፡፡ በክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት ፣ የአረጋዊያንን ቤት በመጠገን ፣በከተማ ጽዳትና ደም በመለገስ ተግባራት መሳተፉን ጠቅሷል፡፡ " በበጎ ተግባር ላይ ሁሉም ወጣት በመሳተፍ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ፈለግ መከተል አለበት" ብሏል፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ምህንድስና ተማሪ መቅደስ ኢናሮ በበኩሏ በሃገር ደረጃ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ስራ በመደገፍ በከተማው የጽዳት ዘመቻ ላይ ከጓደኞቿ ጋር ለመሳተፍ መወሰኗን ተናግራለች፡፡ " ጊዜና ጉልበት እያላኝ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ አድርጌ አላውቅም"  ያለችው  ተማሪዋ አሁን ላይ ባከናወነችው ስራ ሰዎች ተደስተው በማየቷ መርካቷን ተናግራለች፡፡ በሶዶ ከተማ መርካቶ ክፍለ ከተማ መናፈሻ መንደር በበጎ ፈቃድ ወጣቶች የመኖሪያ ቤት በአዲስ መልክ ከተሰራላቸው መካከል  ወይዘሮ አዮሜ አዳቾ አስታዋሽና ጧሪ አጥተው ባሉበት ሁኔታ ወጣቶች ያደረጉት ድጋፍ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ዝናብና ጸሃይ ሲፈራረቅባቸው በችግር ያሳለፉትን ጊዜ አስታውሰው ወጣቶቹን ባደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በዞኑ ቦዲቲ ከተማ ጮጫ ቀበሌ የሚገኘው አርቲስት ካሳ አላሮ " በዓለም የተለያዩ ሃገራትን በመዞር ለሃገሪቱና አከባቢው ብዙ የሰራሁ ቢሆንም  አስታዋሽ አጥቼ ቆይቻለሁ "ብሏል፡፡ በወጣቶቹ የተደረገው ድጋፍና መነሳሳት ሃገርን ማዳን እንደሚችልና የነበረውን ቅሬታ በማስወገድ ተስፋ እንዲሰንቅ እንዳደረጋው ተናግራል፡፡ የወላይታ ዞን ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ሚካኤል ዋዳ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው አቅመ  ደካሞችን በማገዝ ከጎናቸው መሆናችንን የማሳየት ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የተቸገሩ ነዋሪዎችን በመለየት ቤት የመገንባትና የመጠገን ስራ መከናወኑንም ጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይ በአዲሱ ዓመት ፍቅርና መተሳሰብን በመስበክ በሀገሪቱ የተገኘው ለውጥ ለማጠናከር  እንደሚደግፉ በአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ከነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኒማ ዙበር እንዳሉት አዲሱን ዓመት በደማቅ ሁኔታ ለመቀበል ተዘጋጅተዋል፡፡ " በቅርቡ አሶሳ ከተማ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ አይገልጽም"  ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በከተማው ያለውን የብሄር ብሄረሰቦች መከባበር ለማድፍረስ ያለመ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ወደቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ መመለሷን ጠቅሰው " በአዲሱ ዓመት አሁን የተፈጠረው ሰላማችን እንዲቀጥል እሰራለሁ" ብለዋል፡፡ " ልጆቼን በሚገባ መምከር፣ የተጣሉና የተቀያየሙ ወዳጅና ጎረቤት ማስታረቅ በግሌ ተግባራዊ ለማድረግ ያቀድኳቸው ናቸው "ሲሉም አክለዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የአንድነት ጉዞና በጎ ተግባር በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ በከተማው የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አደም ካሣው ናቸው፡፡ " የምናስበው ድህነትን አስወግደን ልማትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እንዲስፋፉ ነው" ያሉት  አስተያየት ሰጪው ህግና ስርዓት ማክበር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ የልማት ዋነኛ ኃይል የሆነውን ወጣቱን ለልማት እንጂ ለጥፋት እንዳይተባበር በመምከርና በማስተማር ሃገራዊ ለውጡን ዘላቂ ለማድረግ እንደሚደግፉም ጠቅሰዋል፡፡ ሰላም ከሁሉም ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን የተናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መንግስቱ ታፈሰ " መንግስት የያዘውን የሰላም፣ የፍቅርና የይቅርታ አቅጣጫ እንዲጠናከር  እሰራለሁ" ብለዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የወላይታ ዞን አስተዳደር ወላጆቻቸውን ላጡ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ችግረኛ ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ድጋፉን በሰጡበት ወቅት " የተቸገሩትን ማገዝና ከጎናቸው መሆናችንን ማሳየት የየትኛውም የኃይማኖትና ፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የሌለበት የሰብአዊነት ግዴታ ነው" ሲሉ ገልጿል፡፡ ድጋፉን ያገኙ ወላጆችና ተማሪዎች የዞኑ አስተዳደርንአመስግነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም