ቁርጠኛና ብቃት ያለው አመራር ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል

96

ባህር ዳር ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) በየደረጃው ቁርጠኛና ብቃት ያለው አመራር ለማፍራት ለስትራቴጂካዊ አመራር ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

"አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ፤ አዲስ ሀገራዊ እምርታ" በሚል መሪ ሀሳብ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ትናንት ማምሻውን በክልሉ የተለያዩ ከተሞች መስጠት ተጀምሯል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ በባህርዳር ከተማ ስልጠና መክፈቻ ላይ እንዳሉት፣ በሁሉም ዘርፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሩ ወቅቱን ያገናዘበ ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል።

በየደረጃው የሚሰጠው ስልጠና አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታን  በአመራሩና በአባላት ውስጥ እንዲሰርጽ ከማድረግ ባለፈ ሀገራዊ ዕምርታን ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከብልፅግና ጉባኤ ማግስት የመንግስት አስተዳደር ስርዓቱን ለማጠናከር በየደረጃው ሲሰራ መቆየቱንም ገልፀዋል።

የመንግስት አስተዳደር ስርአቱን ለማጠናከርም ቁርጠኛና ለህዝብ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚችል ብቃት ያለው አመራር መገንባት እንደሚያስፈልግና ስልጠናው ለእዚህ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ግርማ እንዳሉት በስልጠናው ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተለያዩ አምስት የስልጠና ማዕከላት ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በቀጣይም ስልጠናውን እስከ አባላት ድረስ ለማድረስ መሰል መድረኮች እንደሚዘጋጁ የገለጹት አቶ ግርማ፣ "ይህም በእውቀት ላይ ተመስርቶ የተሟላ አመራር ለመስጠት ያግዛል" ብልዋል።

ሰልጣኞች በስልጠናው የሚያገኙትን እውቀትና ከህሎት ተጠቅመው የመንግስትን ተልዕኮን በአግባቡ መወጣትና ህዝብን በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም