የኦሮሚያ ክልል አዲስ ዘመን መቀበያን ምክንያት በማድረግ ከ5 ሺ በላይ የህግ ታራሚዎችን በይቅርታ ለቀቀ

137
አዲስ አበባጳጉሜ 5/2010 የኦሮሚያ ክልል አዲስ ዘመን መቀበያን ምክንያት በማድረግ ለ5 ሺህ 325 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ። የክልሉ ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት የክልሉ መንግስት የህዝብ ወገንተኝነትን የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰዱን አጠናክሮ ይቀጥላል። ይህንኑ መርህ መሰረት በማድረግም ነው በዛሬውም እለት የክልሉን ህገ መንግስት መሰረት በማድረግ  ፕሬዝዳንት ለማ  መገርሳ 5 ሺህ 325 በይቅርታ እንዲለቀቁ ወስነዋል ብለዋል። እርምጃው የተወሰደው አዲሱን ዓመት በሰላምና በፍቅር ለመቀበል ካለው እሳቤ በመነሳት ነው ብለዋል። በዚህ አጋጣሚ ''ወደ ቤታቸው ለተመለሱ ታራሚዎችና ቤተሰቦቻቸውም እንኳን ደስ አላችሁ'' ብለዋል ዶክተር ነገሪ ሌንጮ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ40 ሺህ የሚልቁ የህግ ታራሚዎችን በይቅርታና በምህረት ከማረሚያ ቤት እንዲለቀቁ አድርገዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም