የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

47

ሰኔ 1/2014/ኢዜአ/ የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ፌስቲቫሉ ከሰኔ 7 እስከ 12/2014 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት በወዳጅነት ፓርክ ይካሄዳል ተብሏል።  

በፌስቲቫሉ 11 የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሚሳተፉ ሲሆን አውደ-ጥናት፣ በአውደ-ርዕይ እንዲሁም የኪነ-ጥበብና የስፖርት መርሃ ግብሮችን ያካትታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በሰጡት መግለጫ፤ ፌስቲቫሉ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።

ፌስቲቫሉን ኢትዮጵያ ማስተናገዷ የአገሪቱን ባህል አጉልቶ ለማሳየት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ፌስቲቫሉ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሚሰባሰቡበት አጋጣሚን ይፈጥራል ብለዋል።

የባህል ዲፕሎማሲን ለማሳደግና የኢንቨስትመንት ልውውጥን ለማሳለጥም እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።  

የጥበባትና ባህል ፌስቲቫሉ "ባህልና ጥበባት ለቀጠናዊ ትስስር" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም