የቋንቋ ቀንን ማክበር የሰዎችን ባህል፣ ሥልጣኔ፣ ሰብዓዊነትና ሉላዊነት በአንድነት እንደማክበር ይቆጠራል

69

ሰኔ 1/2014/ኢዜአ/ የቋንቋ ቀንን መዘከር የሰው ልጆችን ባህል፣ ሥልጣኔ፣ ሰብዓዊነትና ሉላዊነት በአንድነት እንደማክበር ይቆጠራል ሲሉ የመንግሥታቱ ደርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ተናገሩ።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስድስት ይፋዊ የሥራ ቋንቋዎች አንዱ የሆነው የሩስያ ቋንቋ ወይም ሞስኮኛ ቋንቋ ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከብሮ ውሏል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 ነበር የሩሲያ ቋንቋ በየዓመቱ እንዲከበር ውሳኔ ያሳለፈው።   

የሩስያ ቋንቋ ቀን የሩስያ ዘመናዊ ሥነ-ጽሁፍ አባት ተብሎ በሚወደሰው ዕውቁ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን ልደት ጋር በማስተሳሰር የሚከበር ቀን መሆኑም ይታወቃል።  

የመንግሥታቱ ደርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2018 ጀምሮ ቀኑን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየዘከረው ይገኛል።  

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ የሩስያ ቋንቋ ቀን የመከበሩ ዓላማ የብዝሃ ቋንቋና የብዝሃ ባህልን ታሳቢ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የመንግሥታቱ ድርጅት የሥራ ቋንቋዎችን እኩል አገልግሎት ለማስፋፋት ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቋንቋ ቀናትን ማክበር የሰዎችን ባህል፣ ሥልጣኔ፣ ሰብዓዊነትና ሉላዊነት በጋራ እንደማክበር ነው ያሉት ምክትል ዋና ፀሃፊው፤ ሩስያ ቋንቋም የሩስያዊያንን ሥልጣኔ፣ ባህልና ሥነ-ጽሁፍን ያቀፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ለብዝሃ ቋንቋ ዕድገት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም እንደ ሥራ ቋንቋነቱም በተቋሙ በቤተ-መጻሕፍት ውስጥ የሩስያ ቋንቋ ክፍል ማደራጀቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም ፍላጎት ላላቸው ሰራተኞች የሩስያ ቋንቋ እንዲማሩ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የሩስያ ሳይንስና ቋንቋ ማዕከል ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን ብዝሃ ቋንቋና ብዝሃ ባህልን ለማስፋፋት ቀኑ እንደሚከበር ገልጸው፤ ቋንቋ የሰው ልጆች መግባቢያና የዓለማችን መንፈሳዊና ባህላዊ ሥልጣኔዎች ቅርሶች አካል እንደሆነ ተናግረዋል።

በዕለቱም በመላው ሩስያ የሚከበረው የቋንቋ ቀን የታሪክና ባህል ማንነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚናገረው ሩስያኛ ቋንቋ ሥነ-ጽሁፍ ወደ በርካታ ቋንቋዎች መተርጎሙና በኢንተርኔት አገልግሎትም ሁለተኛው ከፍተኛው አገልግሎት የሚሰጥ ቋንቋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሩስያ ቋንቋና ዕውቀትን ለኢትዮጵያዊያንና በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሌሎች ዜጎች ዘንድ ለማስፋፋትም በአዲስ አበባ የፑሽኪን የሳይንስና ባህል ማዕከል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሩስያ ቋንቋ በዓለማችን በስፋት ከሚነገሩ ቋንቋዎች አንዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ200 ሚሊዮን በላይ ተናጋሪዎች አሉት።

በመድረኩ የሩስያን የቱሪዝም ጸጋዎች የሚያሳዩ መረጃዎች ለታዳሚው ቀርበዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም