በአሸባሪው ህወሃት አፈና እና እንግልት ውስጥ ያለው የትግራይ ክልል ህዝብ ለህልውናው ሲል ቡድኑን ተደራጅቶ ሊታገለው ይገባል

173

ሰኔ 1/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሃት አፈና እና እንግልት ውስጥ ያለው የትግራይ ክልል ህዝብ ለህልውናው ሲል የሽብር ቡድኑን ተደራጅቶ ሊታገለው እንደሚገባ የትዴፓ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ ገለጹ።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሙሉብርሃን ሃይሌ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ ህዝብ በአሸባሪው ህወሃት እየደረሰበት ያለው ግፍና በደል ተባብሶ ቀጥሏል።

አሸባሪው ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅትም ቢሆን ለትግራይ ክልል ህዝብ የፈየደው አንዳችም መልካም ነገር ሳይኖር በችግርና አፈና ሲያስተዳድር እንደነበር አስታውሰዋል።

ከምስረታው ጀምሮ ህዝብን  በማግለልና በመነጣጠል የራሱን ዓላማ የሚያሳኩ ካድሬዎችን ብቻ በዙሪያው በማሰባሰብ የህዝብን ድምጽ አፍኖ የኖረ የጥፋት ቡድን ስብስብ ስለመሆኑም አቶ ሙሉብርሃን ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን አሸባሪ ቡድኑ አፈናውን አጠናክሮ በመቀጠል የክልሉን ህዝብ ለከባድ ችግርና እንግልት እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በህዝብ ትግል ከስልጣን ከተወደገ በኋላ .እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ ትፍረስ. ብሎ በመነሳት በጥፋቱ ቀጥሎበታል ብለዋል።

ዓላማውን ለመፈፀም የኢትዮጵያን ህልውና ከማይፈልጉ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ በመስራት የክህደቱን ጥግ በማሳየት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ከትግራይ ክልል ባለፈ በአጎራባች ክልሎችም ጭምር የጸረ ህዝብ እንቅስቃሴ በማድረግ ለዳግም ወረራ እራሱን እያደራጀ ይገኛል ነው ያሉት።

በመሆኑም የአገር ጠላት የሆነውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን በጋራ መታገል ይገባል ያሉት አቶ ሙሉብርሃን በተለይም በአፈና እና እንግልት ውስጥ ያለው የትግራይ ክልል ህዝብ ለህልውናው ሲል በመደራጀት ታግሎ እንዲያስወግደው ጥሪ አቅርበዋል።

የሽብር ቡድኑ ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን ሰብአዊ እርዳታ በመቀማት ለዓላማው ማስፈፀሚያ ለሚያሰልፋቸው ታጣቂዎች እያዋለ ስለመሆኑም ግልጽ መሆኑን ተናግረዋል።

''የትግራይ ህዝብ ተራበ ሞተ ጉዳዩ አይደለም'' የሚሉት አቶ ሙሉብርሃን  የክልሉ ህዝብ ለህልውናው ሲል ተደራጅቶ ሊታገለው ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም