አገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን የህብረተሰቡን ነባር ዕውቀት መጠቀም ይገባል

88

ሚዛን አማን ሰኔ 1/2014 (ኢዜአ)  አገራዊ ምክክሩን ለማሳካት የህብረተሰቡን ነባር ዕውቀት መጠቀም እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የህዝብ ባህል፣ ወግና ነባር እውቀቶቹን ተንተርሶ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የበኩላቸውን ትብብር እንደሚያደርጉም ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል።

የካፋ ዞን የአገር ሽማግሌ አቶ አሰፋ ገብረማርያም ኢትዮጵያ የበርካታ ነባር እውቀቶች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው "ህዝቦቿ ደግሞ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው ያውቃሉ" ብለዋል።

የአገር ሽማግሌዎች ከሌሎች አካላት በበለጠ ተሰሚነትና ክብር ያላቸውና ችግር የመፍታት አቅም ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሚያካሂዳቸው ተግባራት በእነዚህ ታግዞ ነባር ዕውቀቶቹን እንዲጠቀምባቸው ጠይቀዋል።

እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ዓላማ ለማሳካት የህዝቡን ባህላዊ እሴቶች ከራሱ የአሰራር ስርዓት ጋር አጣምሮ መጠቀም አለበት።

ውይይትና መፍትሄ ለማፈላለግ ከራስ ብቻ ተዘጋጅቶ ከመምጣት አስቀድሞ ህዝቡ ምን አለው? የሚለውን ተረድቶ ባህልና ወጉን መሠረት ያደረጉ መረጃዎችን ማጥናት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በምክክሩ "ማኅበረሰቡን የሚመስል አቀራረብ መፈጠር አለበት" ያሉት አቶ አሰፋ፣ "እንደ አገር ሽማግሌና የህብረተሰብ ባህልና ወግ አዋቂ ኮሚሽኑን ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

"የእኛን ችግር እኛና የእኛ እውቀት እንጂ የፈረንጅ ጥበብ ሊፈታው አይችልም" የሚል አቋም እንዳላቸውም አስረድተዋል።

የኮንታ ዞን የአገር ሽማግሌ ሻምበል ጀበሎ ቡላ በበኩላቸው የአገራዊ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ኢትዮጵያን ጠንቅቀው የሚያውቁና በሳል በመሆናቸው ለአገራዊ እሴቶቹ ቦታ ይሰጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ እውነተኛ እርቅ የሚፈጠርበትንና ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ለማምጣት ወደ ኅብረተሰቡ ዘልቆ በመግባት የማኅበረሰቡን ታሪክና እሴት አካቶ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉም አሳስበዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ትላልቅ ፈተናዎች በየቦታው ሲያገጥሟት ፈተናውን በመቆጣጠር በሰላም የሚኖሩ አካባቢዎች ዘንድ በመድረስ የእነርሱን ተሞክሮ መቀመርም የኮሚሽኑ ተግባር እንዲሆን ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የማኅበረሰቡን እውነተኛና ነባር ማንነት በማሳወቅ ትብብር እንደሚያደርጉም በማረጋገጥ።

የቤንች ሸኮ ዞን የአገር ሽማግሌ አቶ ሰለሞን ኮዥቴት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሰላምና አንድነቷን አስጠብቃ የቆየችባቸው አገር በቀል ዕውቀት እንዳላት መስክረዋል።

ዜጎች አገራዊ ችግሮችን በጋራ ተመካክሮ መፍትሄ ማፈላለግ እንደማያዳግታቸውም አመልክተዋል።

ሁሉም ብሔረሰብ በሚያምንበትና በሚጠቀመው ባህላዊ የእርቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ዘመናዊውን በማከል ከተሰራ መልካም ውጤት ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የጥንቱን ኢትዮጵያዊ መልካም ማንነት በማንጸባረቅ ችግሮችን ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ድጋፍ እንዲደረግለትም አቶ ሰለሞን ጠይቀዋል።

በየአካባቢው ያለውን እውነት በማሳየት ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን መደገፍ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የባህልና ወግ ባለቤቶች ግዴታ መሆኑን አመልክተው፣ ራሳቸውም ሚናቸውን ለመጫወት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም