22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጀመረ

585

ሰኔ 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሞሪሺየስ በሚካሄደው 22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ተጀምሯል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 28 ሴት እና 26 ወንድ በድምሩ 54 አትሌቶችን ታሳትፋለች።

በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን ኢትዮጵያን አትሌቶች በተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮች ይካፈላሉ።

በ100 ሜትር ሴቶች ራሔል ተስፋዬ እና ያብስራ ጃርሶ፣በ400 ሜትር ሴቶች ፅጌ ዱጉማ፣ አማረች ዛጎና ምስጋና ኃይሉ፣በ400 ሜትር ወንዶች ዮብሰን ብሩ እና ዮሐንስ ተፈራ እንዲሁም በ100 ሜትር ወንዶች ሎቾ ኪዮንጋ ኢትዮጵያን ይሳተፋሉ።

በኮት ዶአር ናሽናል ስፖርት ኮምፕሌክስ ስታዲየም በሚካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከ35 በላይ የአትሌቲክስና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች እንደምትሳተፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በሞሪሺየስ በሚካሄደው 22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ42 አገራት የተወጣጡ 636 አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሻምፒዮናው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2018 በናይጄሪያ አሳባ በተካሄደው 21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 የወርቅ፣ሶስት የብርና አምስት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎች በማግኘት አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት 21ዱም የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተሳትፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም