በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ የህዝብና የጭነት ተሸከርካሪዎችን ለመመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ ነው

103

ግንቦት 30/2014/ኢዜአ/ በመዲናዋ የሚንቀሳቀሱ የህዝብና የጭነት ተሸከርካሪዎችን በመመዝገብ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።

ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉንም ቢሮው አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ይርጋለም ብርሀኔ፤ የታሪፍ ማሻሻያውንና አጠቃላይ የትራንስፖርት ስርአቱን ለመምራት እተየከናወኑ ያሉ ተግባራትን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በመዲናዋ የሚንቀሳቀሱ ማናቸውም የህዝብ መገልገያዎችንና የጭነት ተሸከርካሪዎችን መዝግቦ መቆጣጠር የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሚወጣውን መመሪያ አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት የሚደረግበት መሆኑንም ሃላፊው ገልጸዋል።

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን መሰረት በማድረግ ከነገ ጀምሮ በሚኒ ባስ እና በሚዲ ባስ ተሸከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የታሪፍ  ማሻሻያ ስለመደረጉም ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት በተደረገው ማስተካከያ ከ50 ሳንቲም እስከ 3 ብር ከ50 ሳንቲም ጭማሪ ስለመደረጉ አብራርተዋል።

ከታሪፍ ማስተካከያ በላይ ክፍያ የሚጠይቁ አገልግሎት ሰጭዎች ካጋጠሙ ማህበረሰቡ ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቅ አስገንዝበው ህግን ተላለፍው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎቱን የተሳለጠ፣ አሰራርና ደንብን የተከተለ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት የማህበረሰቡና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲጠናከር ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም