ከ2015 የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ውስጥ 400 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል--አቶ አህመድ ሽዴ

169

ግንቦት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከ2015 የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ውስጥ 400 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ፡፡

ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌዴራል መንግስት የ2015 ዓ.ም ረቂቅ የበጀት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

ረቂቅ የበጀት እቅዱን ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ ረቂቅ በጀቱ የተዘጋጀው ከባለበጀት መስሪያ ቤቶች ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የረቂቅ በጀቱ ዝግጅት በ2014 በጀት ዓመት የነበሩ አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታዎችና የቀጣይ ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

May be an image of one or more people and indoor

በዚህም በቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት እንደሚያሳይና አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታው ሰላማዊ እንደሚሆን ታሳቢ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የተያዘ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 218 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ለካፒታል በጀት መመደቡን ጠቅሰዋል፡፡

345 ነጥበ 1 ቢሊዮኑ ለመደበኛ ወጪ፤ 209 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ ደግሞ ለክልል መንግስታት ድጋፍ እንደሚከፋፈልም አብራርተዋል፡፡

ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል ነው ያሉት፡፡

ከተመደበው በጀት ውስጥ 400 ቢሊዮኑን ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ገልጸው፤ ይህም ከ2014 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ36 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አለው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም