በገላን ከተማ ከ76 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ልማት ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በገላን ከተማ ከ76 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ልማት ገብተዋል

አዳማ ግንቦት 30/2014(ኢዜአ)--- በገላን ከተማ ከ76 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ልማት መግባታቸውን የከተማዋ አስተዳደር ገለፀ።
የገላን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ወይንሸት ግዛው ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማዋ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት ዓመት ከ76 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ልማት መግባታቸውን ገልጸዋል።
አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ቡና ማቀነባበሪያን ጨምሮ ሌሎች የአምራች ኢንዱስትሪ መስኮች ደግሞ ኢንቨስተሮቹ የተሰማሩባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ወደ 177 ባለሀብቶች እንደተሰማሩ አመልክተዋል።
ከእነዚህም ወደ ስራ የገቡ የኢንቨስትመንት ተቋማቱ ከ23ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
መስተዳድሩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከማመቻቸት ባለፈ በቂ መሬትና መሰረተ ልማት በማዘጋጀት ለባለሀብቶች ማስተላለፉን ወይዘሮ ወይንሸት ገልፀዋል።
የገላን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለቤት አቶ አብዱልሃኪም ሙሀመድ በበኩላቸው ከገላን ከተማ አስተዳደር 28 ሄክታር መሬት ተረክበው ወደ ልማት መግባታቸውን ነው የተናገሩት።
ከገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በአዳማ ቆርቆሮና ብረታ ብረት ፋብሪካ የማስፋፊያ ስራ አጠናቀው ወደ ምርት መግባታቸውንም አክለዋል።
የገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ከጀመሩ ሶስት ወር መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የሼዶች ግንባታ በፍጥነት በማከናውን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ካፒታላቸው አጠቃላይ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የተናገሩት አቶ አብዱልሃኪም በገላን ላይ ዘርፈ ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የገላን ከተማ አስተዳደር በመሬት፣ በመሰረተ ልማትና በአንድ ማዕከል አገልግሎት አቅርቦት ቀልጣፋ በመሆኑ ለስራችን ውጤታማነት የተሻለ አቅም ሆኖናል ሲሉም አክለዋል።
የገላን ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ "የክልሉ መንግስት ለተሰማራንበት ኢንቨስትመንት ተገቢውን እገዛ እያደረገልን ነው" ያሉት ደግሞ የሆራ ትሬዲንግ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መላኩ ናቸው።
በገላን ከተማ በወጪ ንግድና በቡና ማቀነባበሪያ ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን የገለፁት ምክትል ሃላፊው፤ በተለይ በመሬት አቅርቦት እንዲሁም የተፋጠነ አገልግሎት እንዲገኝ ከማድረግ አንፃር አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጅታቸው ከ1ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑት ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።
በገላን ከተማ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በክልሉ መስተዳድር፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ፣ በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር እንዲሁም በቋሚ ኮሚቴዎቹ ሃላፊዎች በቅርቡ በከፊል መጎብኘቱ ይታወሳል።