ለአገር ግንባታና ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ለአገር ግንባታና ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል

ግንቦት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)ለአገር ግንባታና ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የጋራ ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ከንቲባዋ በልደታ ክፍለ ከተማ 36 የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ዛሬ አስጀምረዋል፡፡
በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤የልማት ሥራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ በጥረት የተደገፈ ቀጣይነት ያለው ሥራ ከሁላችንም ይጠበቃል።
ለአገር ግንባታና ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሁሉም ማኅበረሰብ የጋራ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች በባለሀብቶችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክፍለ ከተማው በዛሬው እለት 36 የንግድና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 28 የንግድ ቤቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የመኖሪያ ቤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለግንባታው አጠቃላይ ወጪ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሚጠይቅ ሲሆን በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ፤ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች ላይ ተቋማቸው በመሳተፉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በክፍለ ከተማው የምገባ ማዕከል ግንባታ እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ አበባ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሊደግፉ የሚችሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል፡፡