በአምስት የተለያዩ ቋንቋዎች የጤና መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል አገልግሎት ተጀመረ

172


አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጤና መረጃዎችን በአምስት የተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል አገልግሎት መጀመሩን ብሄራዊ የህብረተሰብ ጤና አደጋ የመረጃ ማዕከል ገለጸ።የዲጂታል መረጃ አገልግሎቱ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች ተደራሽ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል።


የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ፤ የመርሃ ግብሩን ይፋ መደረግ ተከትሎ ባስተላለፉት መልእክት ኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ አቅሙን ለማሳደግ ከመስራቱ ባሻገር የምርምር ስራዎችንም እያካሔደ መሆኑን ተናግረዋል።


የኮቪድ 19 መከሰትን ተከትሎ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በ8335 የተለያዩ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም የጥሪ ማዕከሉን አቅም በማሳደግ 120 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ እንዲችል መደረጉን ተናግረዋል።


የዝንጀሮ ፈንጣጣ፣ የኮቪድ 19፣ ጊኒወርም፣ ቢጫ ወባና ኮሌራን የተመለከቱ መረጃዎች በጥሪ ማዕከሉ ለህብረተሰቡ እንደሚደርስ ነው ያስታወቁት።


የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጎማ በበኩላቸው ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠርና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በዘርፉ ውጤታማ ስራዎች እየተካሔዱ መሆኑን ገልጸዋል።


በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ዲጂታል ሲስተምም የጤና መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።


የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ በጥሪ ማዕከሉ እስካሁን 3 ሚሊዮን ሰዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ አቅሙን በማሳደግ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ለማስተናገድ እንዲችል ተደርጓል ብለዋል።


የጥሪ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ሲያከናውኑ የነበሩትን የህብረተሰብ ጤና ቅኝት በስልክ ለማስተላለፍ ያስችላልም ተብሏል።


በተመሳሳይ በአምስቱ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ድረገጽ ይፋ ተደርጓል።


የዲጂታል ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተጀመረ ሲሆን የገንዘብ ወጪዉን ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን እንደሸፈነው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም