በመዲናዋ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት አስፈጻሚ አካላት መደበኛ ተግባራቸው አድርገው እንዲሰሩ ተጠየቀ

37

ግንቦት 29/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት አስፈጻሚ አካላት መደበኛ ተግባራቸው አድርገው እንዲሰሩ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር ምክር ቤት እና የትብብር ጥምረት አሳሰበ።

የትብብር ጥምረቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው የመጀመሪያ የምስረታ ጉባኤ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የወጡ ሁለት መመሪያዎችን ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር ተወያይቶ አጽድቋል።

መመሪያዎቹ የትብብር ጥምረቱ አሰራር የሥራ ቡድኖች እና አደረጃጀት እንዲሁም የተጎጂዎች የቅብብሎሽ ሥርዓት መመሪያዎች መሆናቸው ታውቋል።

የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ በኃላፊነት የሚመራው በሰዎች የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል126/2014 አዋጅ መጽደቁ ይታወቃል።

በዛሬው እለት የጸደቀው መመሪያ አዋጅ 126/2014ን ወደ ሥራ ለማስገባትና በከተማዋ ያሉ አስፈጻሚ ተቋማት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በቀጥታ እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ጽዋዬ ሙሉነህ ገልጸዋል።

''በሰዎች የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር ላይ የሚሰራ ምክር ቤት እና የትብብር ጥምረት ቢሮው ማቋቋሙንም ተናግረዋል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በአገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ አዲስ አበባ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆኑ መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ከሕግ አስከባሪ ተቋማት ባሻገር የከተማዋ አስፈጻሚ ተቋማት ችግሩን በመገንዘብ በተለየ ትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎችም የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዋና መነሻ የሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎችን በመለየት ከክልሎች ጋር መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ በመመሪያው ሊካተት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአገር ውስጥ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር በመመሪያው ቢካተት ሲሉ ጠይቀዋል።

ለስደት ተመላሾች የተሃድሶ ተቋማትን በቋሚነት ማቋቋም፣ በቂ የሥራ እድሎች እንዲኖራቸው  ማስቻልና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች አንስተዋል።

ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በመለየት በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።

በሰዎች የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር ምክር ቤት እና የትብብር ጥምረት ሰብሳቢና ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፤ የምክር ቤት አባላቱ የሰጧቸው ግብዓቶች አጽንኦት ይሰጣቸዋል ብለዋል።

በዋናነት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል የአገር አቀፍ አጀንዳ ቢሆንም አዲስ አበባ ላይ በልዩ ሁኔታ መሥራትና ለመቀነስ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተሰጡት አስተያየት መሰረት አስፈጻሚ ተቋማት ከተልኳቸው አኳያ እንዲሰሩ ለማድረግ መመሪያውን በድጋሚ የመፈተሽ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸው፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመደበኛ ሥራቸው አካል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም