በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው ቋንቋዎችን ለማበልጸግ እየተሰራ ነው

121

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ ስጋት የተደቀነባቸውን ቋንቋዎች በመለየት የመሰነድና እንዳይጠፉ የማበልጸግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ 50ኛ ዓመት የጥናትና ምርምር ጉዞውን የሚዘክር ክብረ-በዓል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ አክብሯል።

የአካዳሚው ዳይሬክተር ዶክተር ዮሐንስ አድገህ በዚሁ ወቅት፤ አካዳሚው በኢትዮጵያ ያሉ ቋንቋዎች እና ባህሎች እንዲበለጽጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለትውልድ እንዲተላለፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ ትምህርትና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በአገሪቱ ሰላሳ የሚደርሱ ቋንቋዎች ለመጥፋት አደጋ ስጋት የተጋለጡ መሆናቸው መለየቱን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አንድ ቋንቋ ከትውልድ ወደ ትውልድ ካልተላለፈ፣ ዝቅተኛ ተናጋሪዎች ካሉት እና በሌሎች የቋንቋ ማበልጸጊያ ሂደቶች ጥቅም ላይ ካልዋለ የመጥፋት አደጋ ውስጥ መሆኑን ያሳያል።

በዚህም የሥርዓተ-ጽህፈት የሌላቸውን ቋንቋዎች እንደ ቋንቋ ባህሪያቸው በጥናት ላይ በመመስረት በግዕዝና በላቲን ፊደላት ሥርዓተ-ጽህፈት የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

አነስተኛ ተናጋሪ ላላቸው ቋንቋዎች ጭምር መዝገበ-ቃላት በማውጣት ቋንቋዎቹ ከአፍ መፍቻነት ባለፈ ለትምህርት መስጫነት እንዲውሉ አካዳሚው የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቋንቋዎቹ እንዳይጠፉ በጽሑፍ የመሰነድ እና በሌሎች የቋንቋ ማበልጸጊያ ስልቶች እንዲዳብሩ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የተናጋሪዎቹ ሕዝብ ባህል እንዲታወቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።

ባህሎቻችንና ቋንቋዎቻችንን በማልማት ለማኅበረሰብ አገልግሎት ያላቸውን ፋይዳ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ናቸው።  

በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ የአገረ-መንግሥት ግንባታ ውስጥ ሕብረ-ብሔራዊ የሆነ አገር ለማጽናት ቋንቋዎችና ባህሎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም