በኢትዮጵያ 53 ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ለመማር ማስተማር ውለዋል- ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

47

ግንቦት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ 53 ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ለመማር ማስማር መዋላቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ማዳበር የሚያስችል ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱንም ገልጿል።

ሁለተኛው አገር አቀፍ የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ጉባኤ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተጀምሯል።

ጉባኤው የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ለአገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ያለው ፋይዳና ለመንግስት የቋንቋዎች ፖሊሲ ግብአት የሚውሉ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ እንደተዘጋጀ ተነግሯል።

የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ባህልና ቋንቋ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ቋንቋዎቿን ለማልማትና ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ውስጥ 53ቱ ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ለትምህርት አገልግሎት መዋላቸውንና በቀጣይም የቋንቋዎቹን ቁጥር ለመጨመር መታሰቡን ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የጸደቀውን የቋንቋ ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የቋንቋ ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ለማሳደግና ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴርና ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ላለፈው አንድ ዓመት በጉዳዩ ላይ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን አመልክተዋል።

በጥናቱ ምክረ ሀሳብ አማካኝነት የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ለማዳበርና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል መነሻ ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን ነው ወይዘሮ ብርቅነሽ ያብራሩት።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ተሾመ አብዶ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለማህበራዊ፣ኢኮኖሚና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳዎች ለማዋል እያደረገ ያለውን ጥረት በጥናትና ምርምር እያገዘ ይገኛል ብለዋል።

የቋንቋዎች ልማት እንዲሁም የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ማጎልበት በቀጣይ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት አስመልክቶ የተዘጋጁ ጥናቶችና የምርምር ስራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም