የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጎልበት በቅንጅት እየተሰራ ነው

82

ግንቦት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጎልበት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ሕብረት የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በጂኦ-ተርማል ኅይል ማመንጫ ዘርፍ ተሰማርተዋል።

በቅርቡም ከጂኦ-ተርማል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለማቋቋም ውል መፈራረማቸውን እና ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህም የፈረንሳይ ኢንቨስትመንት ፈንድ ከጂኦ-ተርማል 150 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ባላት እምቅ የማዕድን ሀብት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ በቀጣይነት እንሰራለን ነው ያሉት።

የማዕድን ሚኒስቴር ከሰሞኑ አደራጅቶ ለሕዝብ ክፍት ያደረገው የማዕድን ጋለሪም ለዘርፉ እምርታ ትልቅ ስኬት እንደሚኖረው ጨምረው ገልጸዋል።

የማዕድን ጋለሪው የኢትዮጵያን የከርሰ-ምድር እምቅ ሀብት በማሳየት በዘርፉ ለሚሰማሩ መረጃ እንደሚሰጥም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም