ባለፉት ዘጠኝ ወራት 932 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ችግኝ ተሸፍኗል

69

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2014 /ኢዜአ/ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 932 ሺ ሄክታር መሬት በቡና ችግኝ መሸፈኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጸረ-ተባይ ኬሚካል የሚረጩ የአምስት አውሮፕላኖችና 23 ድሮኖች ግዥ መፈጸሙንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሑሴን የ2014 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርታቸውም ባለፉት ዘጠኝ ወራት  932 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ችግኝ መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት አመቱ 708 ሺህ ኩንታል የቡና ምርት ለመሰብሰብ ካቀደውም 652 ሺህ ኩንታል መሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡

ምርታማነቱም በሄክታር 7.5 ኩንታል መድረሱን ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡

ከሌሎች ቡና አምራች አገራት አኳያ ቡናን በማልማት ረገድ በርካታ ስራዎች የሚቀሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግል ባለሃብቱን በማሳተፍ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የሰብል በሽታዎችና ተባይ በዘርፉ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል አምስት የርጭት አውሮፕላኖች እና 23 ድሮኖች ግዥ መፈጸሙን ገልጸዋል

የጸረ ተባይ ኬሚካል ማከማቻ መጋዘን ግንባታም 95 በመቶ መጠናቀቁን ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ገልጸዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ጥገና ለማካሄድ ለክልሎች 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

እነዚህ ጥረቶች በየጊዜው ዘርፉን እየፈተነ ያለውን የድህረ ምርት ብክነት ለመቀነስ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል፡፡

የግብርና ምርቶችን ጤንነት ጥረትና ደህንነት አረጋግጦ ወደ ውጭ በመላክ ረገድ 682 ሺህ ቶን ምርት ላይ ምርመራ ተደርጎ እንዲላክ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም