በሰሜን ወሎ ዞን የኢንዱስትሪ ልማትን መሰረት ያደረገ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

82

ወልድያ፣ ግንቦት 27/2014(ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን የኢንዱስትሪ ልማትን መሰረት ያደረገ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ መስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ መስተዳድር "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ቃል ከባለሃብቶችና ሌሎች አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በወልዲያ ከተማ ተወያይቷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋው ባታብል በውይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት ሀገራችን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ዘርፎች አንዱና ዋነኛው የኢንዱስትሪ ዘርፉ ነው።

በዞኑም የግብርናው ዘርፍ የሚያቀርበውን ምርትና የማዕድን ዘርፉን በግብዓትነት የሚጠቀም የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የቆቦ ጊራና የመስኖ ልማትንና የተከዜ ተፋሰስን በማማከል በእንሰሳት፣ በሰብል፣ በእጽዋትና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶችን በማበረታት የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪውን ለማጠናከር አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።

በማዕድን ዘርፉም በድንጋይ ከሰል፣ በከበረ ድንጋይ (ኦፓል)፣  የሲልክ፣ አሸዋ፣ እብነበረድ፣ ብረትና ወዘተ. የማዕድን ዘርፎች በመሰማራት የኢኮኖሚክ እድገት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰሜን ወሎ ዞን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ካላቸው ዞኖች አንዱ በመሆኑ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ዋና አስተዳዳሪ ጠይቀዋል።

የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማስፋፋትም ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ለባለሃብቱ ምቹ የሆነ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ከባለሃብቶች መካከል ኢንጂነር የኋላው ሲሳይ በሰጡት አስተያየት ባለሃብቶችን ወደ ዞኑ በመሳብ የሚፈለገውን የኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ በደብረ ብርሃን የታየውን መልካም አሰራር መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

"ወልድያ ከጅቡቲ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል" ያሉት ኢንጅነር የኋላው በአካባቢው ያለውን ፀጋ የማስተዋወቅ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ የመጡት ባለሃብት ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ በበኩለቸው ባለሃብቱ ክልልና ዞን ሳይገድበው ወደ ሰሜን ወሎ እንዲመጡና ከመጡም እንዳይወጡ ለማድረግ የተለየ የአመራር ጥበብ መከተል ያስፈልጋል ብለዋል።

አመራሩና ባለሙያው የተናበበና የተቀናጀ መልካም መስተንግዶ ከሰጡ ሰሜን ወሎ በሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ውስጥ ገብተው ለመስራት ራሳቸውም ሆኑ መድረኩ ያልተገኙ ባለሃብቶች ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ እንዳሉት ባለፉት 27 ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ባለሃብቱና መንግሥት መገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

አሁን ባለሃብቶች ወደ ሰሜን ወሎም ሆነ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በመግባት ማልማት የሚችሉበት ምቹ መደላድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ለአምራች ኢንዱስትሪና ለግብርናው ኢንቨስትመንት የሚሆን ከ1 ሺህ 732 ሄክታር በላይ መሬት ከሶስተኛ ወገን በማጽዳት ተከልሎ እንደሚገኝ ከዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በውይይት መድረኩ በዞኑ የሚገኙ የወረዳና የከተሞች አመራሮች፣ ባለሃብቶች፣ የባንክ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም