በሲዳማና በደቡብ ክልሎች የተከሰተውን የተምች ወረርሽን ለመከላከል እየተሰራ ነው

92

ሃዋሳ፣ሶዶ ግንቦት 27/2014 (ኢዜአ) በሲዳማና በደቡብ ክልሎች የተከሰተውን ተምች የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የክልሎቹ ግብርና ቢሮዎች አስታወቁ ፡፡

የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ቦልካ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በልግ አብቃይ በሆኑ 15 ወረዳዎች “ አፍሪካን አርሚ ዎርም ” እና “ፋል አርሚ ዎረም ” የተሰኙ ሁለት አይነት ተምች ተከስቷል።

“አፍሪካን አርሚ ዎርም ” የተሰኘው መደበኛው የተምች አይነት ሲሆን፤ በክልሉ በሚገኙ 15ቱም ወረዳዎች ሲከሰት፤“ፋል አርሚ ዎረም ” የተሰኘው መጤ ተምች ደግሞ በዘጠኝ ወረዳዎች መከሰቱን አስታውቀዋል።

በክልሉ ከሁለት ሳምንታት በፊት የተከሰተው ይኸው ተምች እስካሁን ከ6 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የበቆሎ ሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

በክልሉ የተከሰተው ተምች የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በባህላዊ ዘዴና በኬሚካል ርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት እስካሁን በተሰራው ስራ 4ሺህ 520 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተከሰተውን ተምች በባህላዊ ዘዴና በኬሚካል ርጭት ማስወገድ ተችሏል።

ኬሚካል ርጭቱ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያስከትል እንደ ጎመንና ቦሎቄ ካሉ ደባል ተክሎች ነፃ በሆነና የከፋ ጉዳት በደረሰበት የበቆሎ ማሳ ላይ በጥንቃቄ መካሄዱን አስረድተዋል።

ለኬሚካል ርጭት ጥቅም ላይ እንዲውል 3ሺህ 927 ሊትር “ማላታይን” የተሰኘ ፀረ-ነፍሳት ኬሚካል መቅረቡን ጠቅሰው እስካሁን 1 ሺህ 200 ሊትር ያህሉ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።

ተምቹን በመከላከሉ ሥራ የግብርና ባለሙያዎችና ተማሪዎችን ጨምሮ ከ19 ሺህ በላይ  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የበልግ እርሻ 36ሺ 158 ሄክታር ማሳ በበቆሎ መልማቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በሶዶ ዙሪያ፣ ዳሞት ጋሌ፣ በዳሞት ፑላሳና በዳሞት ወይዴ ወረዳዎች የተከሰተው ተምች በቆሎና በግጦሽ ሳር ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ገልጸዋል።

በወረዳዎቹ  የተከሰተው መደበኛ ተምች ከ480 ሄክታር በላይ በሆነ የሰብልና ግጦሽ መሬት ላይ በተለይ ሰፋፊ ቅጠል ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

ተምቹ በጋራ የሚያጠቃ፣ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ አርሶ አደሩ በየቀኑ ማሳውን በመፈተሸ እንዲከላከለውና ሲከሰትም የቤተሰብ አባላትን በማስተባበር በባህላዊ መንገድ እንዲያጠፋው አሳስበዋል።

እንዲሁም ተምቹ ወደ እርሻ ማሳ እንዳይገባ 50 ሳንቲ ሜትር ጥልቀትና ስፋት ያለው ቦይ በመቆፈር ወደ ቦዩ ሲገባ አዳፍኖ መግደል፣ በመስክ ላይ ደግሞ በመጨፍጨፍና በከብቶች በማስረገጥ ሊከላከለው ይገባል ብለዋል።

ተምቹን በባህላዊ ዘዴ መቆጣጠር ሳይቻል ሲቀርም ፀረ-ተባይ ኬሚካል ርጭት በማድረግ የመከላከሉ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን በመከላከል ሥራ መሰማራታቸውን ገልጸው፣ አርሶ አደሩም የባለሙያዎችን ምክር ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በዞኑ በበልግ እርሻ በቦቆሎ፣  በድንች፣  በአደንጓሬ፣  በቦሎቄ  እና በሥራ ሥር ከለማው ከ111 ሺህ  ሄክታር በላይ መሬት ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም