በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሃት ያወደማቸውን ተቋማት መልሶ ግንባታ ስራዎች በትኩረት መከናወን አለባቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

127

ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሃት በወረራ ያወደማቸውን ተቋማት መልሶ ግንባታ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው መከናወን እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስገነዘቡ።


በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመራ የፌደራል መንግስት የስራ ሃላፊዎች ቡድን ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።


የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን በወረራው ምክንያት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገውን የሰብአዊ አቅርቦት የተመለከተ የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።


በክልሉ ተፈጽሞ በነበረው ወረራ የተነሳ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዉ እርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸዉን ገልጸው፤ ከተለያዩ አጋር አካሎች ጋር በመሆን ለተፈናቃዮቹ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።


የሚቀርበዉ እርዳታ ከተረጂዎች ቁጥር አንጻር በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ የአሸባሪው ህወሃት ሀገር የማፍረስ አላማ ቅዠት ሆኖ እንዲቀር የአፋር አናብስቶች ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያዉያን ጋር በመሆን በታሪክ የማይረሳ ተጋድሎ ፈጽመዋል።


የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ወረራ እርዳታ ጠባቂ ለመሆን የተገደዱ ዜጎችን ለመደገፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካሎችን በማስተባበር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።


ከእለት ደራሽ ሰብአዊና የስነ-ልቦና ድጋፉ ጎን ለጎን እየተካሄደ ያለው የወደሙ ተቋማት መልሶ ግንባታ መጠናከር እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።


የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸዉ አሸባሪው ህወሃት ወረራ ፈጽሞባቸው የነበሩ አካባቢዎች አዛውንት፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና ሴቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።


ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችንና የመጠጥ ውሃ ተቋማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጉዳት ማስተናገዳቸውን አስታውሰዋል።


ይሁንና አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ትኩረታቸውን በትግራይ ክልል ላይ በማድረጋቸው በአፋርና አማራ ክልሎች ለችግር የተጋለጡ ተፈናቃዮች በቂ ድጋፍ ሳያገኙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።


ይህንን በሚመለከት በመንግስት በኩል ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ ተከታታይ ገለጻ በመደረጉ የአለም አቀፍ ተቋማቶች የተዛባ አመለካከት እንዲታረምና ትክክለኛዉ እውነት እንዲገነዘቡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።


በዚህም በክልሉ ለተፈናቀሉ ሰዎች የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አበረታች ጅምሮች መኖራቸዉን አንስተዋል።


በጦርነት የተጎዱ ተቋማትን ወደስራ ለማስገባት የተጀመረዉ የመልሶ ግንባታ ስራ ላይ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎ እንዲያደርግ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም