በማዕድን ሚኒስቴር የተገነባው የኢትዮጵያ ማዕድን ጋለሪ ተመረቀ

456


ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በማዕድን ሚኒስቴር የተገነባው የኢትዮጵያ ማዕድን ጋለሪ ተመረቀ።

በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ኡርን ጨምሮ የዲፕሎማቲኩ ማህበረሰብ ፣ የዘርፉ አልሚዎችና ባለሀብቶች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።


የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ የማዕድን ሀብት ዋነኛ የዕድገት አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።


ከዛሬ ጀምሮ ለጎብኝዎች ክፍት የሚደረገው ለባለሀብቶች የኢንቨስትመንት አማራጭ ማሳያ ጋለሪው ዘርፉን የማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ማዕድን ጋለሪ የማዕድን መረጃን በቴክኖሎጂ ታግዞ ያከማቸ ሲሆን የጋለሪው ጎብኝዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን በአይነትና በመገኛ ስፍራዎች በቀላሉ እንዲረዱ ያስችላል።


በምርምር ዘርፉም ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብም ጋለሪውን በመጎብኘት ስለማዕድናት ግንዛቤ እንዲጨብጡ በሚያደርግ አግባብ የተዘጋጀ ነው።


በማዕድን ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም ለግብዓትነት የሚያገለግል እንደሆነ ተገልጿል።


የማዕድን ጋለሪው ከተቋሙ ሪፎርም ስራ ውጤቶች መካከልም አንዱ ሲሆን ጋለሪውን ለማደራጀትም ግማሽ ዓመት እንደፈጀ ታውቋል።


ጋለሪውን ለማደራጀት የማዕድን ዘርፍ ኩባንያዎች ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።


በዚህም በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩና በጋለሪው መቋቋም አስተዋጽኦ ያደረጉ ኩባንያዎች በማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ዑማ ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም