ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተዘረፉ የመብራትና የስልክ ገመዶችን ደብቆ የተገኘው ግለሰብ በ ጸኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

108

ጎንደር፤ ግንቦት 27/2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተዘረፉ የመብራትና የስልክ ገመዶችን በመኖሪያና በንግድ ቤቱ ደብቆ የተገኘው ግለሰብ በ3 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣቱን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የፍርድ ቤቱ የኮሙዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሮ ማስተዋል ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት ቅጣቱ የተላለፈው እውነቱ ሞላ ፈንቴ በተባለ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው፡፡

ተከሳሹ የተዘረፈ የመንግስት ንብረት በመሸሸግ በከባድ ወንጀል በአቃቢ ህግ ክስ የተመሰረተበት መሆኑን ተናግረዋል።

 በተከሳሹ መኖሪያና የንግድ  ቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ግምታቸው ከ635 ሺህ ብር በላይ  የሚያወጡ የመብራትና የስልክ ገመዶችን  በድብቅ ተከማችተው መያዛቸውን የአቃቢ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳ ገልጸዋል፡፡

በተከሳሹ በአቃቢ ህግ የተመሰረተበትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ክስ ክዶ ተከራክሯል፡፡

 ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ተከሳሽ የቀረበበትን ክስና ማስረጃ ሊያስተባብል ባለመቻሉ ግንቦት 26/2014 ዓ.ም  በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ  ተከሳሹ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለበትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት በመያዝ በ3 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና የ2 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ወስኖበታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም