ቀጥታ፡

ለውጡ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል-የሶማሌና የሐረሪ ክልላዊ መንግስታት

ጅጅጋ/ሀረር ጳጉሜ 5/2010 በህብረተሰቡ ውስጥ የይቅርታና የመቻቻል ባህል እንዲጎለብትና የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ  የሶማሌና የሐረሪ ክልላዊ መንግስታት አስታወቁ ። አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት  ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስተፌ ሙሀመድ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦች በይቅርታና በመቻቻል የወንድማማችነት ግንኙነትታቸውን እንዲያጠናክሩ ይሰራል ብለዋል። የክልሉ ህዝብ በለውጡ ሂደት ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖረው በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል ። በክልሉ ከሙስና ከአድሎ፣ ከወገንተኝነትና ከጎሰኝነት የፀዳ አሰራር በማስፈን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ አዲሱ አመራር ለገባው ቃል ተግባራዊነት ህብረተሰቡ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ። "በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አከባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በአዲሱ ዓመት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ክልሉ ከኦሮሚያ ጋር በትብብር ይሰራል " ብለዋል ። አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የብልጽግናና የእድገት እንዲሆን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  ምኞታቸውን ገልፀዋል ። በተመሳሳይ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሀዲ የክልሉ ህዝብ መገለጫው የሆኑትን የሰላም፣ የፍቅርና አብሮ የመኖር እሴቶችን በአዲሱ ዓመት በማጠናከር ሀገራዊ ለውጡን እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ። "የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣አባ ገዳዎች የክልሉን ሰላምና የተጀመረውን ለውጥ ከማስቀጠል አኳያ ድርሻቸው የጎላ በመሆኑ በአዲሱ ዓመትም ሚናቸውን ማጎልበት ይገባቸዋል " ብለዋል ። " ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ ናት" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የለውጥ መገለጫዎች የሆኑና አልፎ አልፎ እየተከሰቱ ያሉ አለመረጋጋቶች ሙሉ ለሙሉ እየከሰሙና ሰላማዊ እንቅሰቃሴ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል ። የክልሉ ህዝብ ሰላምን በማጎልበት ሀገራዊ ለውጡን በተጠናከረ መልኩ መደገፍና ማስቀጠል እንዲችል የክልሉ መንግስት በትኩረት እንሰሚሰራ አስታውቀዋል ። ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣የአንድነት፣የለውጥና የፍቅር እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም