መገናኛ ብዙኃንና የማህበረሰብ አንቂዎች በትውልድ ስነምግባር ግንባታ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል

53

ግንቦት 26 ቀን 2014(ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃንና የማህበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ተደማጭነታቸው ሰፊ ስለሆነ በትውልድ ስነምግባር ግንባታ ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመለከተ።

የጉባኤው ዋና ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በልጆች ምግባር ላይ ለውጥ ለማምጣት ከመምህራን፣ ከትምህርት ማህበረሰቡና ከሃይማኖት አባቶች ጋር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

ምክክርና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችንን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እንደሆነ ጠቁመው፤ የሃይማኖት አባቶች በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በማቅናት ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲበረቱና በስነ ምግባራቸው እንዲጎለብቱ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።

ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ቤት እንደማሳለፋቸው መጠን ሰፊ የስነ ምግባር ቀረጻ ስራ እንደሚስፈልግ የተናገሩት ዋና ጸሐፊው፤ የአዲስ አበባ ትምህር ቢሮን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትምህርት ቤቶች ዙርያ የሚታዩ ሁኔታዎችን ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።

በስርዓተ ትምህርት ውስጥ አገር በቀልና ሃይማኖታዊ እሴቶቸ እንዲካተቱ ለማድረግም ጉባኤው እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ነው መጋቢ ታምራት የተናገሩት።

ወላጆች ልጆቻቸውን በግብረገብነት አንጸው እንዲያሳድጉ ለማድረግ ጉባኤው ለሃይማኖት መምህራን ስልጠና በመስጠት ጉዳዩን በአስተምህሯቸው እንዲያካትቱ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል መገናኛ ብዙኃን፣ የማህበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ተደማጭነታቸው ሰፊ ስለሆነ በትውልድ ስነምግባር ግንባታ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

የአንድ ትውልድ የስነ ምግባር ግንባታ የሁሉንም አካላት ርብርብ ስለሚጠይቅ መንግስት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች ኢትዮጵያዊ ሰብዕናንና አብሮነትን ያከበረ ስራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

Description: ‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም