ሕብረተሰቡ ለልብ ሕሙማን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማዕከሉ ጥሪ አቀረበ

158

ግንቦት 26/2014/ኢዜአ/  ሕብረተሰቡ ለልብ ህሙማን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ጥሪ አቀረበ፡፡

በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆነችው ጋዜጠኛ ህይወት ታደሰ ልደታቸውን በማስመልከት ከማኅበራዊ ሚዲያ ያሰባሰቡትን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በዛሬው ዕለት በተወካያቸው በኩል ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህጻናት መርጃ  ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ህሩይ አሊ አስረክበዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚሁ ወቅት ማዕከሉ ከተቋቋመ 34 ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ባለፉት 14 ዓመታት ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የልብ ህሙማን ህክምና አገልገሎት ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡

የማዕከሉ መቋቋም ወደ ውጭ አገር ሄደው የሚታከሙ ህሙማን በአገር ውስጥ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉንም ነው ያነሱት፡፡

ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ሥራዎች መልካም ጅማሮ ቢያሳዩም አሁንም ማዕከሉ የሰዎችን እገዛ እንደሚሻ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ጋዜጠኛዋ ልደቷን አስመልክቶ ለማዕከሉ ላደረገችው ድጋፍ አመስግነው ይህ እንቅስቃሴዋ ቀጣይነት እንዲኖረው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማእከሉ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመሆን ሕብረተሰቡ በአጭር የጽሁፍ መልክት ህሙማንን የሚያግዝበት አሰራር ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ በማንቀሳቀስ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ኀብረተሰቡ ለማዕከሉ በሚያደርገው ድጋፍ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሳምሶን አደራ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ያለበትን የግብአት ችግር መቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም ለማዕከሉ እገዛ ለሚያደርጉ አከላት ሁኔታዎች በማመቻቸት የማዕከሉን አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የጋዜጠኛዋ የቤተሰብ አባል የሆኑት ወይዘሮ ሮማንወርቅ ታደሰ በበኩላቸው፤ ማህበራዊ ሚዲያን የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ ከመጠቀም ይልቅ ለመልካም ነገር ልናውለው ይገባል ሲሉ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋዜጠኛዋ ቤተሰቦች፣ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል አመራሮች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ለታካሚዎች ነጻ የልብ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም