ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ከመንግሥታቸው ጎን በመሆን የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ መትጋት አለባቸው - የአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ ትሮይ ፊትሬል

አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 ኢትዮጵያዊያን ከመንግሥታቸው ጎን በመሆን በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ መሥራት እንዳለባቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ ትሮይ ፊትሬል አሳሰቡ። አሜሪካና ኢትዮጵያ በመካከላቸው ያለውን ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ቀጠናዊ አጋርነት ለማጠናከር በኢትዮጵያዊያን አዲሱ ዓመት በትኩረት ይሰራሉ ሲሉም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ ትሮይ ፊትሬል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ የሚስተዋለው የለውጥ ጅማሮ አስደሳች ነው። የፀረ-ሽብር ህጉንና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅን ለማሻሻል መንግስት የጀመረው ጥረትና በውጭ አገሮች በስደት ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ወደአገር እንዲመለሱ መደረጉ የሚበረታታ መሆኑን ጉዳይ ፈፃሚው ገልፀዋል። ''የለውጥ እንቅስቃሴው የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት መሰረት መሆኑን የአሜሪካ መንግስት ያምናል'' ያሉት ጉዳይ ፈፃሚው፤ ይህ ይጠናከር ዘንድም መላው ኢትዮጵያውያን ከመንግሥታቸው ጋር በመሆን በኃላፊነት እንዲሰሩ ሀሳብ ሰጥተዋል። የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን አልፎ ስኬት እንዲመጣ ሕዝቡ ተስፋ ሳይቆርጥ በጽናት ከመንግሥት ጎን ቆሞ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። “ የእኔ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞቴ፤ ይህንን አዲስ እድል (ለውጡ) ለመጠቀም ሕዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት የሚል ነው፤ ይህንን እድል በመጠቀም አገሪቱ ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ አለባቸው፤ እድሉ ያለፈውን መቀጣጫ ለማድረግ መሆን የለበትም፤ በአዲሱ ዓመት እንደገና ለመጀመር እድል ይሰጣል፤ አዲሱ ዓመት በነገሮች ላይ ለመወያየት፣ ሙግት ለማድረግና አድናቆትም ለመስጠት እድል ይሰጣል፤ በአገሪቱ በመንግሥት የተጀመረውን የለውጥ ሥራ ወደፊት ለማስጓዝም ሕዝቡ ለመተባበር እድል ይሰጣል፤ ምክንያቱም መንግሥት የሚሰራው ሥራ የህዝቡን ሥራ በውክልና በመሆኑም ሕዝቡ በስፋት መሳተፍ አለበት “ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የተሻለ የመናገር ነጻነት መኖሩን ጉዳይ ፈፃሚው ጠቁመው ይህንና ሌሎች የፖለቲካ መብቶችን ለማጠናከር ለመብቶቹ ተቋማዊ እውቅና መስጠትና በሕግ ማስደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ መላው ሕዝብ የተጎናፀፈውንና አገሪቱን ወደፊት ሊያራምድ በሚችል መልኩ የተፈጠረውን የመናገር ነጻነት መብት በጥንቃቄና በኃላፊነት ስሜት መጠቀም የዜጎች ግዴታ መሆኑን አሳስበዋል። “ለኢትዮጵያውያን የምመክረው ነገር ቢኖር አዲሱን ነጻነት በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል፤ ነጻነቱንም በኃላፊነት መጠቀም ያስፈልጋል፤ ወጥተህም ልትናገር ስትል ኃላፊነት ልትወስድ ይገባል፤ በተለይም ንግግርህ ውጤታማ፣ ትክክልና አገሪቷን ወደፊት ሊያራምዳት መቻሉን ማረጋገጥ አለብህ “    ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ መብቶች ተከብረው ሕዝቡ ተጠቃሚ የሚሆነው በአገሪቱ የምጣኔ ኃብት እድገት ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑንም አስምረውበታል ትሮይ ፊትሬል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚያደርጋቸው የፖለቲካ ለውጦች ጎን ለጎን ለምጣኔ ኃብት እድገት በተለይም በሥራ ፈጠራ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። “ኢትዮጵያውያን የሚፈልጓቸውን የፖለቲካ መብቶች ለማስፋት ተቋማዊ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፤ በተለይም የመሰብሰብ፣ የመናገር ነጻነት፤ የተቋማት ነጻነት፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ መብቶች ለማረጋገጥ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አገር ውስጥ የምጣኔ ኃብት እድገት ሳይመጣ ለመመለስ አይቻልም፤ በመሆኑም የምጣኔ ኃብት አድገት፤ የሥራ እድል ፈጠራ ያስፈልጋል፤ በመሆኑም በዚህም ረገድ በርካታ ሥራ መሠራት አለበት “ የአሜሪካ መንግስት ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ማኅበራዊ ልማትን ለማጠናከር በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኃብት በማፍሰስ በጋራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። በአዲሱ ዓመትም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ይህንን የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ ጉዳይ  ፈፃሚ ትሮይ ፊትሬል አረጋግጠዋል። ''አሜሪካ  ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የምትሰራው አገሮቹ የጋራ አቋም ያላቸው በመሆኑ ነው ''ያሉት ምክትል አምባሳደሩ ይህም ለቀጠናውም ጭምር አዎንታዊ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የኢትዮጵያና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመረው አጼ ምንሊክና የአሜሪካው ልዑክ ሮበርት ስኪነርና እ.ኤ.አ 1903 የንግድ ሥምምነት ከፈረሙ ጊዜ አንስቶ ነው። አሜሪካ ከኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋሮች መካከል አንደኛዋ እንደሆነችም ይነገራል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም