የግሉ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆን በትኩረት ይሰራል

59

ግንቦት 26/2014/ኢዜአ/ የግሉ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢትዮ-እስራኤል የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ማሳደግ የሚያስችል ስምምነትና የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ  ተካሂዷል።

በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የንግድና የዘርፍ ማህበራት አመራሮች፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በርካታ ጸጋ እና ሰፊ የሰው ኃይል ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።

ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የተካሄደው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉን እንዲያንሰራራ በማድረግ ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በገንዘብ ተቋማት ላይ የተደረገው ማሻሻያም ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለቱሪዝም፣ ለቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘርፎች ማበረታቻ እንዲደረግ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆንም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"በኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄም የተሻለ የሥራ እድል የሚፈጠርበትን ሁኔታ በማመቻቸት የወጪ ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ካደረጉ የእስራኤል ባለሃብቶች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና እስራኤል ታሪካዊ ግንኙነትን ለማስቀጠልም የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች  በንግድና ኢንቨስትመንት አስተሳስሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሁለቱም ሀገራት ያላቸውን አቅም በማስተሳሰርም ለጋራ እድገት መጠቀም እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፤ የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርና፣ በጤና፣ በፈጠራ እና ሌሎች መስኮች  መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

የእስራኤል ኩባንያና ባለሃብቶች በተጠናከረ መልኩ ኢትዮጵያ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ ስምምነቱ የኢንቨስትመንት ትስስሩን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የፌደራል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፤ ማህበሩ ስምምነቱን የወሰደው የእስራኤል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲጠቀሙበት ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ስምምነቱም የእስራኤልን የተሻለ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምድ በመቅሰም የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

መድረኩ የሁለቱ ሀገራትን የቆየ ጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ግንኙነት እንደሚያስቀጥልም ተገልጿል።

የምክክር መድረኩን የፌደራል ንግድና ዘርፉ ማህበራት እና በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ያዘጋጁት ሲሆን በወቅቱም የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም