በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት መካከል ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ ነው

70

ግንቦት 26/2014/ኢዜአ/ በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት መካከል ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሰባተኛው የጤና ደሕንነት ክብካቤ ጥራትና ደሕንነት ጉባኤ "ቀጣይነት ያለው የጤና አገልግሎት ጥራት እና መማማር ለጥራት ባህል ግንባታ" በሚል መርሕ ተካሂዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ወቅት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ የመሰረተ ልማትና የግብዓት አቅርቦት እየተሟላላቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።

በተለይ ለተቋማቱ የግብዓት አቅርቦት ለማሟላት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በጉባኤው እንደሀገር የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል ለማዘመን እና የተሻለ ለማድረግ በሚያስፈልጉ መስኮች ላይ ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማውጣት የጤና ሴክተሩን በቴክኖሎጂና ግብአት ለማሟላት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ተጠያቂነትን በመዘርጋት ጭምር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ይሕም የተገልጋይ እርካታን ለማምጣት እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት።

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕክምና ጥራት አገልግሎት ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ሻንበል በበኩላቸው፤ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ደረጃ በደረጃ በማሟላት ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን አሁንም የህክምና መሳሪያዎች እጥረት በመኖሩ ምክንያት የጤና ሚኒስቴርና የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው የጠየቁት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም