ህግ የማስከበር ዘመቻው የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅ ነው- የህግ ባለሙያዎች

68

ሐዋሳ፤ ግንቦት 26/2014(ኢዜአ)፡ መንግስት እየወሰደ ያለው ህግ የማስከበር ዘመቻ የህዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቅና ህጋዊ ግዴታው መሆኑን የደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ የህግ ባለሙያዎች ገለጹ ፡፡

በወቅታዊ ጉዳይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ ባለሙያዎች እንደገለጹት  በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የህግ ጥሰቶች መፍትሄ እንዲያገኙ ህዝቡ   ለመንግስት በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው የነበሩትን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ በመንግስት የተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተገቢነት ያለው  ነው ፡፡

ለተጀመረው ህግ ማስከበር ሂደት ስኬታማነት የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ የወንጀልና ፍትሐብሔር ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ዘውዴ ለማ እንደገለጹት የህግ ማስከበር ስራ በዋናነት የሚመነጨው ህዝብ ከሰጠው ይሁንታ በሚገኝ ህጋዊ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡

በምርጫ ሀገር የመምራት ሃላፊነት የተሰጠው መንግሥት ከህዝብ ጋር የሚገባው ማህበራዊ ውል መኖሩን ጠቅሰው፣ የህዝቡን ሰላምና ጸጥታ የማስጠበቅ ግዴታውን እና ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል ብለዋል፡፡

በቅርቡ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ የዘገየ ነው ያሉት አቶ ዘውዴ መንግስትን በምርጫ ካርድ  የመረጠው ህዝብ ጥያቄውን በተደጋጋሚ ሲያሳነሳ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ በህግ ማዕቀፍ የታገዘና ህጋዊ እርምጃ በመሆኑ መቀጠል እንደሚገባውም ተናግረዋል።

በተለይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከመንግስት እውቅና ውጭ አደረጃጀት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱና ህዝብን ላልተገባ እንግልት የሚዳርጉ አካላትን መንግሥት መቆጣጠር አለበት ነው ያሉት፡፡

በአደረጃጀቶቹ ላይ ዝምታን መምረጥ ህገ ወጥነትን ከማስከተል ባለፈ የመንግሥትን ህልውና ይፈታተናል፤ ያሉት አቶ ዘውዴ፣ የፌዴራል መንግሥት በነዚህ አካላት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በየአካባቢው የተፈጠሩ ኢ- መደበኛ አደረጃጀቶችም ሆኑ ትጥቅ ይዞ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ከማስቆም ባለፈ፤ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

ህዝቡ መንግስት የጀመረው ህግ የማስከብር ሥራ ውጤታማ እንዲሆን  ህገ ወጥ አካላትን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን መቆም አለበት ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ህገ ወጥነቶች የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተኑ በመሆናቸው ህግ የማስከበር ዘመቻው ሀገራዊ አንድነቱን ከማጠናከር አንጻር ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልልም በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮችን በፈጠሩ አካላት ላይ የክልሉ መንግሥት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ፍትህ ቢሮ የህግ ጥናት ማርቀቅና ማስረጽ ባለሙያ አቶ ደለለኝ ብሩ በበኩላቸው በሀገሪቱ የሚወጡ ህጎች ሲጣሱ መንግሥታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር እንደሚፈጥሩ አመልክተው፤የህግ የበላይነት ባልተከበረበት ሀገር ጉልበተኞች የበላይ እንዲሆኑ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

መንግሥት ህግ ሲጣስ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነት እንዳለበት አመልክተው፤ ይህን ማድረጉ ዓለም አቀፍ ግዴታውም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

ሰሞኑን የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በሀገሪቱ የወጡ ህጎችን የማስፈጸም ሃላፊነት ላለበት መንግሥት የተሰጠ ህጋዊ ሃላፊነት መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ማስከበር ለሀገር ሰላምና አንድነት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ለውጡን ተከትለው የተሻሻሉ  ህጎችን መሰረት አድርጎ በመስራት የህግ ማስከበር ሥራውን ውጤታማ ማድረግ ከህግ አካላት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

''መንግሥት የጀመረውን ሂደት በሌላ መልኩ መረዳት ተገቢነት የለውም'' ያሉት አቶ ደለለኝ፣ በሰብዓዊ መብት ስም የሚጣሱ ጉዳዮች ካሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሳሰሉ ጠንካራ ተቋማት በሀገሪቱ መፈጠራቸው መዘንጋት እንደሌለበት አመልክተዋል።

የህግ ማስከበር ዘመቻው ውጤታማ ሆኖ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የዜጎችን ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚጠይቅም የህግ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም