የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2015 የፌዴራል መንግስት በጀት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2015 የፌዴራል መንግስት በጀት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

ግንቦት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2015 የፌዴራል መንግስት በጀት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
የፌዴራል መንግስት የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዝግጅት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም አኳያ፣ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን መልሶ ከማቋቋም፣ቀጣይ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎችን ማሳካት ማእከል በማድረግ እንዲሁም የ2015-2019 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፉን መሰረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ፣ለካፒታል ወጪ ብር 218.11 ቢሊዮን እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 209.38 ቢሊዮን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 12.0 ቢሊዮን የተያዘ ሲሆን አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ብር 786.61 ቢሊዮን ሆኖ ቀርቧል፡፡
ከ2014 በጀት ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የብር 111.94 ቢሊዮን ወይም የ16.59 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበለት የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡