ኢትዮጵያ ጤናማ ምድር እንዲኖር ፍትሐዊ ድርሻዋን እየተወጣች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

360

ግንቦት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ ጤናማ ምድር እንዲኖር ፍትሐዊ ድርሻዋን እየተወጣች ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

“እየጨመረ ለመጣው የምድር ከባቢ አየር ፈተናዎች ራሳችንን ዝግጁ ማድረግ አለብን” ብለዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት "ስቶክሆልም +50" በሚል ስያሜ የአካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ በስዊድን ስቶክሆልም ያዘጋጀው ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።

"ስቶክሆልም +50" የዓለም አካባቢ ጥበቃን በማስመልከት በስዊድን የተካሄደውን ጉባኤ 50ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀ ስብስባ ነው።

"ስቶክሆልም +50" ጉባኤን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “ጉባኤው ልማትና ከባቢ አየርን በማስተሳሰር የሚካሄድና ከምድር ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ለማስቀጠል በድጋሚ ቃል የምንገባበት ነው” ብለዋል።

ጉባኤው የምድር ከባቢ አየር የምታስተናግዳቸው ፈተናዎችና ኢ-ሚዛናዊ እድገት እየጨመሩ በመጡበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ በጣም ወሳኝ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

“ለሁላችንም ጤናማ የሆነች ምድር መፍጠር ከፈለግን በትብብር መስራት ይኖርብናል፤ መጪውን ጊዜ የተሻለ ለማድረግ አሁን ያሉንን አስተሳሰቦች መለስ ብለን መመልከት ያስፈልጋል” ብለዋል።

እ.አ.አ በ1972 በስዊድን በተካሄደው የዓለም አካባቢ ጥበቃ ጉባኤ “ስቶክሆልም መግለጫ” በሚል ስያሜ ስምምነት የተደረሰባቸውን ሀሳቦች በነጠላና በጋራ ምን ያህል ተግባራዊ ተደርገዋል የሚለውን ጉዳይ ማጤን እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ፈተናዎችን ለመቋቋም ብሔራዊ ተቋማትን ማጠናከርና የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

“ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫዎች ጤናማ ምድር እንዲኖር ፍትሐዊ ድርሻዋን እየተወጣች ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ለማሳያነት ጠቅሰዋል።

መርሃ-ግብሩ በአራት ዓመት ውስጥ ከ20 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን የመትከል እቅድ ይዞ እ.አ.አ 2019 መጀመሩን ገልጸዋል።

እስካሁን ከ18 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና የዘንድሮው ዓመት የችግኝ ተከላ ሲከናወን በእቅድ የተያዘውን አሃዝ እንደሚያልፍ አመልክተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ኢትዮጵያ ከቀጠናው ጋር ያላትን የትብብርና የወዳጅነት አድማስ እንድታሰፋ በር የከፈተና በአንድነት መንፈስ ያላትን ልምድ እንድታካፍል አድርጓል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

መርሃ-ግብሩ ለሚመጣው ትውልድ ሕልውና መሰረት የሚጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

ፍላጎት ያላቸው አጋሮች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘላቂነት እንዲኖረውና ለሚመጡት ትውልዶች እንዲተላለፍ በጋራ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

"ስቶክሆልም +50" የዓለም አካባቢ ጥበቃ ጉባኤ እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን፤ ጉባኤው በ50 ዓመት ውስጥ አካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ የተከናወኑ ተግባራት፣ የተመዘገቡ ውጤቶችና ያጋጠሙ ፈተናዎች እንዲሁም ቀጣይ መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያም በአካባቢ ጥበቃ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች በዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት እንደምታቀርብ ተገልጿል።

የመጀመሪያው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ እ.አ.አ በ1972 በስዊድን ስቶክሆልም የተካሄደ ሲሆን 26 ነጥቦችን የያዘው የ“ስቶክሆልም መግለጫ” ማውጣቱ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም