የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ከ7 ሺህ በላይ መጻሕፍት አበረከተ

25

ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተለያዩ ቤተ-እምነቶች ያሰባሰባቸውን ከ7 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት አበረከተ።

ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት "ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ" በሚል መሪ ኃሳብ ለአንድ ወር መጻሕፍትን ለማሰባሰብ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተለያዩ ቤተ-እምነቶች ያሰባሰባቸውን ከ7 ሺህ በላይ  መጻሕፍት ለቤተ-መጽሐፍቱ በዛሬው ዕለት አስረክቧል።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ መጻሕፍቱ ከሰባት ቤተ-እምነቶችና ከአማኞቻቸው የተሰባሰቡ መሆናቸውን በመጥቀስ ለቤተ-መጽሐፍቱ አስረክበዋል።

መጻሕፍቱ ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው፣ የፍልስፍና፣ የአስተዳደር፣ በሰላም ግንባታና በአብሮነት ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ጉባኤው አሁን ላይ ከ7 ሺህ በላይ ያሰባሰባቸውን መጻሕፍት  ማስረከባቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ጉባኤው ከሰባቱ ቤተ-እምነቶች ጋር በመተባበር በርካታ ቁጥር ያላቸው መጻሕፍትን አሰባስቦ ለማስረከብ ማቀዱን ጠቅሰው፤ ቤተ-እምነቶችም መጻሕፍት እንዲያሰባስቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትን ወክለው መጻሕፍቱን የተረከቡት ዶክተር ታምራት ኃይሌ፤ ጉባኤው ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

"ቤተ-እምነቶች የእውቀት ማምረቻ፤ የእውቀት ማስተላለፊያ ናቸው።" ያሉት ዶክተር ታምራት በቀጣይ ለማሰባሰብ ያቀዷቸውን መጻሕፍት እንዲያሳኩም አበረታተዋል።

በርካታ ተቋማት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የመጻሕፍት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የመገናኛ ብዙኃንም ለቤተ-መጽሐፍቱ የሕዝብ ድጋፍ እንዳይለይ እያደረጉ ላለው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም