በደቡብ ኦሞ ዞን የተከሰተውን ተምች ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው - መምሪያው

222

ጂንካ ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በአብዛኛው አካባቢዎች የተከሰተውን ተምች ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም በለጠ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች ተምች ተከስቷል።

በዞኑ በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው የተምች ወረርሽኝ በቡቃያ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ 10 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብሎችና ለመኖ አገልግሎት የሚውሉ ቁጥቋጦዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ዋና ዋና ሰብሎች ጤፍና ዳጉሳ ተጠቃሽ ሲሆኑ በቡቃያ ደረጃ ላይ የሚገኙ የበቆሎ ተክልና የመኖ ሳሮች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ወረርሽኙን ለመግታት በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ እየተሰራ ሲሆን መከላከል ያልተቻለውን የኬሚካል ርጭት በማድረግ ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰሞኑን በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ዝናብም የተምች ስርጭቱን በመግታት  ወረርሽኙ በፍጥነት እንዳይዛመት አግዟልም ብለዋል።

የመከላከሉ ስራ ከክልል ጀምሮ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለመከላከል የሚያግዙ ኬሚካሎች በቂ በሚባል መጠን ቢኖሩም የኬሚካል ርጭት መሳሪያዎች  እጥረት እንዳለ ግን ተናግረዋል።

እጥረቱንም ለመቅረፍ በኩታ ገጠም ማሳዎች አርሶ አደሮችን በቡድን በማደራጀት ኬሚካሎችን ተደራሽ የማድረግ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል ።

ከኬሚካል ርጭቱ በተጨማሪ አርሶ አደሮች በባህላዊ መንገድ ወረርሽኙን ለመግታት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአፈር ካብ በመስራት፣ ቦይ በመቅደድና ተምቹን በእንስሳት በማስረገጥ ወደ ሌሎች አከባቢዎች እንዳይዛመት መግታት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም