የተጀመረው የለውጥ ሂደት ዳር እንዲደርስ እንሰራለን-የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረው የለውጥ ሂደት ዳር እንዲደርስ እንሰራለን-የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች
አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ የመጨረሻ ዓላማ እስኪሳካ ድረስ አንታገላለን ሲሉ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ተናገሩ። የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ ዛሬ ጠዋት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይፋዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። አመራሮቹ ለውጡ ሁሉንም ዜጎች ያሳተፈ እንዲሆን ስላደረገም መንግስትን አመስግነዋል። ወደ ሀገር የመጡት ሁሉም ነገር ተስተካክሎ ሳይሆን ከህዝቡ ጋር በመሆን በውይይትና በንግግር ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት መሆኑንም ገልፀዋል። የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ "ወደ ሀገር የገባነው የታገልንለትን ዓላማ ዳር ለማድረስ ነው" ብለዋል። የዜግነት ፖለቲካ በማራመድ ከቂምና ጥላቻ ወጥተን ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንደሚሰሩም ተናግረዋል። ''የመጣነው አሁን የተፈጠረውንና የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ወደታገልንበት የመጨረሻ አላማ ለማድረስ መከፈል ያለንበትን ክፍያ ከፍለን ይህን ለውጥ ሲናፍቅ ከቆየው ማህበረሰባችን ጋር በጋራ የተረጋጋ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን አስቸጋሪ ትግል ለማገዝ ነው። ከቂም በቀል ርቀን ስላለፈው ይቅር ተባብለን ይህችን መከራዋ በእጅጉ የበዛ አገር እንደምንወድ ዜጎቿ ተጋግዘን ከመከራዋ እናውጣት። ከውርደቷ እንታደጋት ሁላችንም በእኩልነትና ነፃነት የእኩልነት መብታችን ተከብሮ አንድነታችን ተጠናከሮ አንገታችንን ቀና አድርገን፣ አጭበርብረንና ሰርቀን ሳይሆን ደክመን በጉልበታችንና በጭንቅላታችን ሰርተን ከብረን ሀገራችንን የምናስከብርበት ስርዓት እንፍጠር ነው የምንላችሁ።" የንቅናቄው ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በበኩላቸው ትግሉ ተጀመረ እንጂ ስላላለቀ ስራ አጥነትን በመቀነስ ዜጎች የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ከመንግስት ጋር እንሰራለን ብለዋል። ''ትግላችን ተጀመረ እንጂ አላለቀም፤ትግላችን የሚያልቀው በመቶ ሺዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደናንተ አይነቶች ተደላድለው የሚኖሩበት፣ያለምንም ስቃይ ነፃነትን አግኝተው ስራ አጥነትን አጥፍተን በየበረሃው ሞትን አቁመን በየባህሩ መስመጥን አቁመን መላው የኢትዮጵያ ወጣቶች በአገራቸው ሰርተው መኖር አግብተው ልጅ ወልደው የልጅ ልጅ የሚያዩበትን ሁኔታ መፍጠር ስንችል ብቻ ነው ትግላችን የሚያቆመው።'' በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮችንና አባላትን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል። በከተማዋ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከአመራሮቹ ጋርበጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ''በከተማችን በአዲስ አበባ የጀመርናቸውን መጠነ ሰፊ ስራዎች ሊያማክሩን፣ ሊያግዙን ከኛ ጋር ሊራመዱ የአገራችን መፃኢ እድል አንድ ላይ ልንወስን አንድ ላይ ተስማምተን ለመስራት ኃላፊነቱን የተረከበው አዲሱ አመራር ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ልገልፅ እወዳለው። ያገሬ ልጆች ከምንም በላይ የማያልፈውን ኢትዮጵያዊነት ይዘን በመካከላችን ያለውን የጥላቻ ግንብ አፍርሰን በትክከለኛው መንገድ ላይ ነንና ከመጣላላት ወደ አንድ መስመር ገብተን አገራችን ኢትዮጰያንና ህዝቦቿን በሚገባ እንድናገለግል አደራ እላችኋለው።''