ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር በትኩረት ሊሰራ ይገባል- አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር በትኩረት ሊሰራ ይገባል- አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

ባህር ዳር፤ ግንቦት 24 /2014 (ኢዜአ)፡ የአማራ ሴቶች ማህበር የሴቶችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባው የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ አሳሰቡ።
ማህበሩ " ሀገር የሚሻገረው በሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ነው!" በሚል መሪ ሃሳብ ሰባተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በባህር ዳር እያካሄደ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳለበት የጠቆሙት ወይዘሮ ፋንቱ፤ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫና ለመቀነስ የጀመረውን ትግል ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
የማህበሩን አባላትም የሚያገኙትን ስልጠና በአግባቡ በመጠቀም ማህበሩን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

''ማህበሩ በቁርጠኝነትናበእውቀት በሚሰራ አመራር ተጠናክሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ይሆናል" ብለዋል።
ማህበሩ የሴት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በቅንጅትእንዲሰራጠቁመው፤ጉባኤው የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥም አሳስበዋል።
የአማራ ሴቶች ማህበር የፆታ እኩልነትን የሚቀበል ማህበረሰብ እንዲፈጠርና ፍትህ የነገሰበት ክልል እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት ታስቦመመስረቱን የገለጹት ደግሞ የማህበሩ ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ሰላማዊት ዓለማየሁ ናቸው።
ማህበሩ በታማኝነት፣በቅንነትና በበጎ ፈቃደኝነት ማህበረሰብን የማገልገል እሴት እንደገነባም ገልጸዋል።
ማህበሩ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ገልጸው፤ ከነዚህም 90 በመቶው አርሶ አደሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ማህበሩን ለስርዓተፆታ መረጋገጥ የሚያደርገው ትግል እንዲቀላቀሉ ለክልሉ ሴት ምሁራን ጥሪ አስተላልፈዋል።
ጉባኤው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተመላክቷል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ በድምጽና ያለድምጽ የተወከሉ 440 ሴቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የአማራ ሴቶች ማህበር ከተመሰረተ 24 ዓመታት ማስቆጠሩን ለመረዳት ተችሏል።