የነዳጅ ድጎማ ማስተካከያው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናን በማይፈጥር መልኩ ይካሄዳል- ባለስልጣኑ

235

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግሥት የሚያደርገው የነዳጅ ድጎማ ማስተካከያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናን በማይፈጥር መልኩ እንደሚካሄድ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ገለጸ።

መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ድጎማም ኢትዮጵያን ለ132 ቢሊየን ብር የእዳ ክምችት እንድትጋለጥ ማድረጉም ተገልጿል።

በባለሥልጣኑ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተሩ አቶ ለገሰ ቱሉ፤ ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤቶቿ ሁሉ ነዳጅን በውጭ ምንዛሬ ግብይት እንደምትገዛ ገልጸዋል።

ነዳጁ አገር ውስጥ ከገባ በኋላም ከተገዛበት ዋጋ በግማሽ ባነሰ ገንዘብ ለግብይት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

ግብይቱም መንግሥት በሚከተለው የድጎማ አሰራር መሰረት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ያሉ ጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃጸር በግማሽ ያነሰና ሰፊ የዋጋ ልዩነት እንዲኖረው አድርጎታል ብለዋል።

ይህ ኢትዮጵያ ለ132 ቢሊየን ብር የእዳ ክምችት እንድትዳረግ ማድረጉንና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባው ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገራት ኮንትሮባንድ እንዲወጣ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ወደ ጎረቤት አገራት በኮንትሮባንድ መልክ የሚወጣው ነዳጅም በአገር ውስጥ የነዳጅ ሥርጭት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ነዳጅ አቅራቢ ግለሰብና ድርጅቶችም የዋጋ ጭማሪ ወዳለበት አካባቢ በመጠቀም የኮንትሮባንድ ንግዱ እንዲስፋፋ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በደቡብና ምስራቃዊ የኢትዮጵያ አቅጣጫ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ያለባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም በጥናት እንደተረጋገጠ አመላክተዋል።

ጥናቱን መሰረት በማድረግም በቀጠናው ለሚገኙ ከተሞች የስርጭት ማስተካከያ ኮታ በማውጣት እንዲጠቀሙ ማድረግ የሚያስችል እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባይቻልም ከጥር 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገው ድልድል 70 በመቶ የሚሆነውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ማስቆም ተችሏል ብለዋል።

ዓለም አቀፉን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪና መንግሥትም የዋጋ ማስተካከያ ሊያደርግ ይችላል በሚል ነዳጅን በማስቀመጥ እጥረት እንዲከሰት በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አገርን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘውን የነዳጅ ግብይት ወጥ ለማድረግም መንግሥት የነዳጅ ግብይትና ሥርጭት ማስተካከያ ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የዋጋ ማስተካከያውም ቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና በማይፈጥር መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ማስተካከያውም ልዩነቱን በአንድ ጊዜ ህዝቡ ላይ መጫን ሳይሆን ጫናውን ታሳቢ በማድረግ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅትና ግለሰቦችም የሚደረገው ድጎማ እንደሚቀጥል ተነግሯል።

የድጎማ ተጠቃሚ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም እስከ ስድስት ወራት ድረስ የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርጉና በሂደት ከ10 እስከ 20 በመቶ በሚወሰን የታሪፍ ማሻሻያ እንዲወስዱ ይደረጋል ተብሏል።

የድጎማው አሰራርም ለጊዜው በደረሰኝ ሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን ቀጣይ ግን በኢትዮ-ቴሊኮምና ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር አማካኝነት እየለማ በሚገኝ ቴክኖሎጂ ቁጥጥር እንደሚደረግበት ተጠቅሷል።

በሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችና ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተነግሯል።

በነዳጅ ህገወጥ ግብይትን ለማስቆም ከጸጥታ አካላት ጋር ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረ ሲሆን ኅብረተሰቡም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴን ሲያስተውል ጥቆማ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዥ ወጪ የተደረገ ሲሆን ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለም በ2015 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ለጠቅላላ ነዳጅ ግዥ ልታወጣ እንደምትችል ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም