የህግ ማስከበር ስራው ህብረተሰቡ ያለስጋት የእለት ተእለት ስራውን እንዲያከናውን አስችሏል--አባ ገዳዎችና የሐይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የህግ ማስከበር ስራው ህብረተሰቡ ያለስጋት የእለት ተእለት ስራውን እንዲያከናውን አስችሏል--አባ ገዳዎችና የሐይማኖት አባቶች

ደሴ ግንቦት 24/2014 (ኢዜአ) የተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ህብረተሰቡ ያለ ስጋት በመንቀሳቀስ የእለት ተእለት ስራውን እንዲያከናውን እድል ፈጥሯል ሲሉ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን አባ ገዳዎችና የሐይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
የከሚሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አባ ገዳ አህመድ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን የአንድነት እሴት ለማፍረስ በቅንጅት በሚሰሩ የጥፋት ቡድኖች በአካባቢዎች በብሔርና እምነት ሽፋን ግጭቶችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ይስተዋላል።
በንጹሃን ላይ የሚፈጸም የግድያ፣ አፈና፣የንብረት ዘረፋና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች በአከባቢው እየተበራከቱ በመምጣታቸው መንግስት የህግ የበላይነት እንዲያስከብር በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን በተጀመረው የህግ ማስከበር ተግባር ተጠርጣሪዎች ለህግ እየቀረቡ ህብረተሰቡም ያለ ስጋት የዕለት ተእለት ስራውን ያለስጋት ከመስራት ባለፈ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሰላም እንዲንቀሳቀስ መልካም ዕድል ፈጥሮለታል፡፡
"ሁከትና ብጥብጥ ለማንም አይጠቅምም" ያሉት አባ ገዳ መሃመድ ህብረተሰቡ ለሰላምና ለአንድነት ሌት ተቀን ከመንግስት ጋር ሆኖ በመስራት በወንጀል የተጠርጠሩትን የመጠቆምና የማጋለጥ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡
"አሸባሪዎኙ ህወሓትና ሸኔ ካደረሱብን ሁለንተናዊ ጥፋት ተምረንና አንድነታችንን ጠብቀን በጋራ ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከሁላችን የሚጠበቅ በመሆኑ የተጀመረው ህግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል፡፡
የህግ የበላይነት ካለመከበሩ ጋር ተያይዞ ግድያና ስርቆት እየተበራከተ በመምጣቱ ለስጋት ተዳርገው እንደነበር የተናገሩት በከሚሴ ከተማ የእስልምና ሐይማኖት መምህር ሼህ ያሲን ሟህሙድ ናቸው።
"አሁን በተጀመረው ህግ ማስከበር ዘመቻ በከተማችን አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ እንደልባችን ወጥተን መግባት ችለናል፣ ህብረተሰቡም ያለ ስጋት ሰርቶ መብላት እንዲችል እድል ተፈጥሮለታል" ብለዋል፡፡
መንግስት የጀመረውን ህግ ማስከበር ዘመቻ በጥንቃቄ አጠናክሮ በመቀጠል ዘላቂ ሰላም ማስፈን ግዴታው ነው ያሉት ሸህ ያሲን ህብረተሰቡን በማስተባበር ለሰላምና ለአንድነት የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር ሁሉም ማገዝ እንዳለበት የገለጹት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሀገረ ስብከት ስራአስኪያጅ መላከገነት ደጀኔ ተስፋዬ በህግ ማስከበር ዘመቻው አንፃራዊ ሰላም እየመጣ ነው ብለዋል፡፡
ግድያ በሚፈጽሙ፣ ቤተ እምነት በሚያቃጥሉና ሌሎች ወንጅሎች የሚሳተፉ አጥፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የመንግስት ግዴታው በመሆኑ በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የደዋ ጨፋ ወረዳ ነዋሪ ሸህ እንድሪስ ሸህ ታጁ እንዳሉት የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ በሰው እና በንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየቀነሱ መጥተዋል፡፡
አሁን እንደ ልባችን ወጥተን መግባት ከመቻላችን ባለፈ በየእምነት ተቋማችን ያለ ስጋት ሃይማኖታዊ ስረአትን መፈጸም ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።
"ሰላምና አንድነታችንም እየተጠናከረ በመሆኑ ህግ ማስከበር ዘመቻውን እንደግፋለን" ብለዋል።
ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አባ ገዳዎችና የሐይማኖት አባቶች አረጋግጠዋል፡፡