በደቡብ ክልል ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል

ሀዋሳ፣ ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ባለፉት 9 ወራት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ ፡፡

በክልሉ በቡታ ጅራ ከተማ ግንቦት 26 የሚካሄደውን የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ አካል የሆነ ክልል አቀፍ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት አስመልክቶ የቢሮው ሃላፊ አቶ ሐልጌዮ ጂሎ መግለጫ ሰጥተዋል።

የቢሮ ሀላፊው በመግለጫቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ ያለውን አቅም በመጠቀም ዘርፉን ለማነቃቃት የሚያግዙ መዋቅራዊ ማሻሻያና ሌሎች የሪፎርም ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ በዘንድሮ ዓመት ስራዎችን ለማሳለጥ በተከናወኑ ተግባራት የኢንዱስትሪ ዘርፍን በቢሮ ደረጃ እንዲደራጅ በማድረግ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ባጠቃላይ 11 ቢሊዮን 90 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ለ244 የግል ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ነው የገለጹት።

ከተሰጡት ፍቃዶች ውስጥ 88 በኢንዱስትሪ፣ 50 በግብርና ዘርፍ ስሆን ቀሪ 106 ኢንቨስትመንት ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እነዚህ ኢንቨስትመንቶች 69 ሺህ 377 ጊዜያዊና 8 ሺህ 201 ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውንም የቢሮው ኃላፊ ጠቅሰዋል።

ሆኖም በአሁን ወቀት በኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም ክልሉ ካለው እምቅ የኢንቨስትምንት አማራጭና ምቹ የሥራ ሁኔታ አንፃር በሚፈለገው ልክ ዘርፉን ማሳደግ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡

የንቅናቄ ፎረሙም በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለይቶ ለመቅረፍና ባለድርሻ አካላትን ይበልጥ አሰናስሎ በመምራት የተሻለ እመርታ ለማስመዝገብ ታልሞ የሚካሄድ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በንቅናቄ ፎረቡ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ፣ የፋይናንስ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም