ከተሞች የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግ ለዜጎች ፍላጎት የሚመጥን ምላሽ መስጠት አለባቸው- ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ

83

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ከተሞች የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግ ለዜጎች ፍላጎት የሚመጥን ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል” ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

“ከንቲባዎች ከተሞችን በእውቀትና ወቅቱን በዋጀ ጠንካራ ራዕይ መምራት አለባቸው” ብለዋል።

"ተግዳሮትን የሚቋቋሙ ከተሞች በኢንተርፕረነርሺፕ የተቃኘ ተግባር ለከተሞች መነቃቃት እና እድገት እና የከንቲባዎች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ሁለተኛው አገር አቀፍ የከንቲባዎች እና የግሉ ዘርፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

መንግስት ለከተሞች ዕድገትና መስፋፋት ለዜጎች ህይወት መሻሻል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገልጸዋል።

ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ሚና ወሳኝ መሆኑንና ለዚህም ከንቲባዎች ከተሞችን በእውቀት፣በልምድና ወቅቱን በዋጀ ጠንካራ ራዕይ መምራት አለባቸው ብለዋል።

ከተሞች የሚሰበስቡትን ገቢ በመጨመርና የኢኮኖሚ አቅምቸውን በማሳደግ ለዜጎች ፍላጎት የሚመጥን ምላሽ መስጠት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

የነዋሪዎች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ፣ኢንቨስትመንት መሳብ እና ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር መስራት እንዳለባቸው ነው ሚኒስትሯ ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው ምክር ቤቱ የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር መጠናከር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው ሚና ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ የስራ ዕድል ፈጠራ፣የመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣የንግድ መሰረተ ልማት፣የከተማ አስተዳደር እና የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ጉዳዮች ለከተሞች ልማት ያላቸው ሚና በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።

በኮንፈረንሱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ኃላፊዎች፣የከተማ ከንቲባዎች፣የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።

በኢትዮጵያ 2 ሺህ 461 ከተሞች እንዳሉና ከነዚህ ውስጥ ፕላን ያላቸው ከተሞች ብዛት 1 ሺህ 862 መሆኑን ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም