የሲቪክ ማህበራት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው

199

አዳማ ግንቦት 23/2014/ኢዜአ/ የሲቪክ ማህበራት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።

ተቋሙ የሲቪክ ማህበራት ብልሹ አሰራርን በመታገልና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ መድረክ በአዳማ ከተማ በማካሄድ ላይ ነው።

የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሀይሌ በሀገራችን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

ሲቪክ ማህበራት በተለይ የህግና የመልካም አስተዳደር ጥሰት እንዳይፈፀም የሚጠበቅባቸውን ሚና ከመወጣት አንፃር የተፈለገውን ያህል እየተንቀሳቀሱ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የህዝብ ብሶት እንዲሰማና የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የሲቪክ ማህበራት የራሳቸውን አስታዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባቸውም ዶክተር እንዳለ አስገንዝበዋል።

"በሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲጎለብት፣ የተሻለ ስነ ምህዳር ለዜጎች እንዲፈጠር አሁንም በጋራ ተቀናጅተን መረባረብ አለብን" ብለዋል ።

በየደረጃው በሚገኙ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ብልሹ አስተዳደርና አሰራሮች እንዲወገዱ በትብብር ከመስራት ይልቅ በተናጥል በመንቀሳቀሳችን የተፈለገውን ውጤት እንዳናመጣ አድርጎናል ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህም ተቋማቱ ከተደራጁበት ዓላማ አንፃር በህዝብ ጉዳይ ውስጥ የራሳቸውን ሚና ያለመወጣት ቸልተኝነት መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የማህበራቱን አደረጃጀትና አሰራሮችን በአዲስ መልክ ከማደራጀት ጀምሮ የማንቃት ስራ መሰራቱን የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ገልጸዋል።

በዚህም የብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት በፊት ከነበረው በበለጠ ራሳቸውን ያደራጁ ቢሆንም የህግና መልካም አስተዳደር ጥሰት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ሚናቸውን ከመጫወት አኳያ ገና ይቀራል ብለዋል።

የብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች በሀገር ግንባታ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መንግሥት አሰራሮችና ህጎችን ከማሻሻል ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወኑን አቶ ፋሲካው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሲቪክ ማህበራት ዕድገት እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው ድርጅቶቹ በማንኛውም ህጋዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ መፍቀዱ ትልቅ ለውጥ ነው ብለዋል።

በተለይ በተቋቋሙበት ዓላማ ላይ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ መንግሥት እያበረታታ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሁንም እገዛው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ድርጅቶችን መንግስት ለመደገፍና ለማገዝ በተለይ ማህበራቱ ከለጋሾች ጥገኝነት እንዲላቀቁና የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዴሞክራሲ ሥርዓትና በሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻችንን ከማበርከት ባለፈ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ብልሹ አሰራር እንዲወገድና የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መስራት አለብን ብለዋል።

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ እንዲከበሩ የብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት ተቋማት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በዚህም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የፀናባትና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር እውን ማድረግ ይኖርብናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም