በዞኑ የተከሰተ ተምች በሰብል ላይ ጉዳት አደረሰ

263

ሚዛን አማን፤ ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ)፡ በቤንች ሸኮ ዞን የተከሰተ ተምች ከ2 ሺ ሄክታር በላይ የበልግ እርሻ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ ለኢዜአ እንደገለጹት በፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው ተምች በዞኑ በጉራፈርዳ ወረዳ ከ2 ሺ ሄክታር በላይ  በሆነ ሰብል ጉዳት አድርሷል።

የተከሰተውን ተምች በባህላዊ መንገድና በኬሚካል እርጭት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ተምቹ በበቆሎ፣ በጤፍ፣ ሩዝና ስንዴ ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል።

200 ሊትር የተምች ማጥፊያ ኬሚካል ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ጠቁመው፤ የኬሚካል መጠኑ ከተምቹ የመስፋፋትና እያደረሰ ካለው ጉዳት  አንጻር በቂ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህም  ተጨማሪ  1 ሺህ ሊትር ኬሚካል ወደ ዞኑ እንዲላክ መደረጉን ተናግረዋል።

በወረዳው ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ የበልግ ሰብል ያለበት የኩታ ገጠም እርሻ ማዕከል መሆኑን ጠቁመው፤  ለተምቹ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር  የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም