ቀጥታ፡

ለአገር መረጋጋትና ለዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 ለአገር መረጋጋትና ለዲሞክራሲተቋማት ግንባታ ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ልዑክ ዛሬ ወደ ሀገር ሲገባ በመንግስት ሀላፊዎችና በሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አቀባበል ተደርጎለታል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሬፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለብዙ ጊዜ ስንጠብቀው ወደነበረው ሰላማዊ ትግል መመለሳችን ደስ ብሎናል ብለዋል። ፖለቲካዊ ለውጥ በማምጣት ወደ ሀገር ገብተን እንድንታገል ያደረገን መንግስትን እናመሰግናለን ብለዋል። ከሁሉም በፊት ሰላማዊ ፖለቲካ ስለሚቀድም ግንቦት ሰባት ከመንግሰት ጋር በመቆም አገርን የማረጋጋትና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። "ከኢህአዴግ ጋር ካለው የለውጥ ኃይል ጋር በጋራ በመቆም የመጣውን ይህንን ለውጥ አንድ መዳረሻ ብቻ ነው ያለው ብለን እናምናለን።ያ መዳረሻ ደግሞ ኢትዮጵያን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊት አገር ማድረግ ነው።እንደዛ ለማድረግ ያለንን አቅም ሁሉ እዛ ላይ እናውላለን። ደረጃ በደረጃ የምንሄድባቸው ጉዳዮች አሉ።መጀመሪያ ማረጋጋት አለብን።ከዚያ በኋላ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ወሳኝ የሆኑ ተቋማት የሚገነቡበት ጊዜ አለ።ከዛ በኋላ ደግሞ የተረጋጋ ዘላቂ ስርዓት የመፍጠር በጣም በጣም ብዙ ስራዎች ናቸው የሚጠብቁን።" አሁን ላይ ወደ ምርጫ ገብቶ ከመፎካከር ይልቅ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በውይይት መፍትሄ የምንፈልግበት ጊዜ ነውም ብለዋል። "አሁን ኢሚዴትሊ ስራችን ነው ብለን የምናስበው ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነን ከመንግስት ኃይሎችም ጋር ሆነን ይሄንን አገር የማረጋጋት ሀላፊነት መወጣት ነው። አሁን የመፎካከሪያ ጊዜ አይደለም።አሁን አቋም ማሳያ ጊዜ አይደለም።አሁን ይሄን አገር አረጋግቶ በሰከነ መንፈስ እንዴት ወደፊት እንደምንሄድ የምናሳይበት ነው።በሁለተኛ ደረጃ የምናየው የጨዋታው ህግ ምን ያህል የሚለውን በሰፊው በውይይት የፖለቲካ ኃይሎች፣የህብረተሰብ ከፍሎች ምንድን ነው የሚሻላት ለዚህች አገር የሚሻላትን ትርጉም ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር ውይይት ይጠይቃል።" በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ውይይት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም