በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ተፈጽሞበት የነበረው የደቡብ ወሎ ዞን በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስቧል

86

ደሴ፣ ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ተፈጽሞበት የነበረው የደቡብ ወሎ ዞን በ2014 በጀት ዓመት 10 ወራት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የበጀት ዓመቱ የገቢ አሰባሰብ ሁኔታ ላይ የባለድርሻ አካላት መድረክ አዘጋጅቶ ዛሬ በደሴ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ጠጄ ከበደ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመው ወረራ የንግድ ተቋማትን፣ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ገቢ የሚያመነጩ ተቋማትና ድርጅቶችን በመዝረፉና በማውደሙ በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

ከንግዱ ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተከናወኑ ስራዎች በበጀት ዓመቱ 10 ወራት 1 ነጥብ 19 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ ዳኛው ዞኑ በሚያመነጨው ኢኮኖሚ ልክ ገቢ በመሰብሰብ ልማትን ለማፋጠን እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተቀረው የበጀት ዓመቱ ጊዜ የታቀደውን ገቢ ለመሰብሰብ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

አሸባሪው ሕወሓት በደቡብ ወሎ ዞን ወረራ በፈጸመበት ወቅት 1 ሺህ 175 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማውደሙንና መዝረፉን ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም